Sunday, 13 October 2013

ው ይ ይ ት ከግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ክፍል ሁለት (ምዕራፍ ኣንድ) (በ-ኣብርሃም ያየህ)


1
ው ይ ይ ት
ከግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ
ክፍል ሁለት
(ምዕራፍ ኣንድ)
ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር የሚደረግ ግኑኝነትና ትብብር ለምን?

(በ-ኣብርሃም ያየህ)
ጥቅምት 1 ቀን 2006 ዓ.ም. (October 11, 2013)
ማስታወሻ፤ በዚህ መጣጥፍ "እኛ" በማለት በብዙ ቁጥር የምጠቅስበት ምክንያት፥ ሃሳቦቹም ሆኑ ድርጊቶቹ የግሌ ብቻ ሳይሆኑ ከኔ ጋር ሆነው የሚታገሉ ሌሎች
ኢትዮጵያዊያኖች (ኣብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች) የተሳተፉበት ስለሆኑ ነው። ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር ስለተደረገው ግንኙነት ታሪክ ባሁኑ ጊዜ እያቀረብናቸው
ያሉ ፅሁፎችም ባገር ቤትና በውጭ ከሚኖሩት ከነዚሁ የትግል ኣጋሮች ጋር በመመካከርና ፅሑፎቹ ከመሰራጨታቸው በፊት እነሱ ኣይተው ኣርትኦት ከሰጡባቸው በኋላ
ነው። በኔ በኩል በግል የተከናወኑ ነገሮች ስጠቅስ ደግሞ በነጠላ ቁጥር "እኔ" በሚል እጠቅሳለሁ።

መ ን ደ ር ደ ሪ ያ
የወያነና የሻዕቢያ ግጭት እንደተከሰተ ለኢትዮጵያ ህዝብና የተቃዋሚ ኃይላት የቀረቡትለት ሶስት ምርጫዎች ነበሩ።
እነዚሁም፤
1. እጅና እግር ኣጣጥፎ ተቀምጦ መመልከት፤
2. በግጭቱ ሳቢያ የተከሰተውን ትርጉም የለሽ ጦርነት መደገፍ፤.
3. ጦርነቱን መቃወምና ሌላ መላምት መፈለግ።

እኔና የትግል ጓዶቼ የመረጥነው በተራ ቁጥር 3 የተመለከተውን ማለትም ጦርነቱን መቃወምና ሌላ ኣክሳሪ ያልሆነ መላምት
መፈለግ የሚለውን ነው። የዚህ መጣጣፍ ዋና ይዘት ይህንን ምርጫ የወሰድንበት ምክንያትና ያከናወንነው ጉዳይ የሚያትት ስለሆነ ከታች
ውለን እንድርበታለን። ስለሆነም፥ የኛውን ምርጫ ለጥቂት ደቂቃዎች ወደጎን ተተን ሁለቱን ምርጫዎች የከተሉትን ዜጎችና ትውልደ
ኢትዮጵያዊያኖችን በተመለከተ ባጭሩ ትንሽ እንወያይ።
እጃቸውና እግራቸው ኣጣጥፈው ስለሚመለከቱ ሰዎች
በመጀመሪያ ተራ ቁጥር የተመለከቱትን ኣስመልክቶ ብዙ መተቸት ኣያስፈልገንም። ምክንያቱም፥ እነዚህ ሰዎች ምንም
ያልሰሩ ሰዎች ስለሆኑ ነው። ምንም ያልሰራ ሰው ደግሞ መውቀስም ማሞገስም ኣይቻልም። ነገር ግን፥ እንደዚህ ላሉ ሰዎች ይህን ኣጋጣሚ
ተጠቅመን የምናስተላልፍላቸው ምክር ኣዘል ወገናዊ መልእክት ኣለን።
2

ላንዳንድ ሰዎች፥ ወይንም ለበርካታ ሰዎች ማለት ይቻላል፥ ኣገር ማለት ጮማ የሚቆርጡበት፥ ጠጅ የሚጋቱበት፥ ለሽርሽር
የሚሄዱበት፥ ወንዙን ተራራውን እየጠሩ በግጥምና በስድ ንባብ የሚመፃደቁበት፥ የሚጨፍሩበትና የሚዘሉበት፥ ወዘተ ብቻ ይመስላቸዋል።
በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ደግሞ፥ ሌላው የፖለቲካ ሱስ ያለበት ይመስል፥ ከፖለቲካ ገለልተኛ ነኝ፥ ፖለቲካ ኣልወድም፥
ሃይማኖተኛ ነኝ፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋጋ የለውም ወዘተ. የሚሉ ጉዶች ኣሉ። ኣንዳንዶቹማ፥ መታገሉንና ላገር መቆርቆሩ ቀርቶ፤
ነብሳቸውን ሸጠው ከሚታገግሉ ሰዎች ጋር ላለመታየት እንኳ ሲንጰረጰሩ ማየት ትውልዱ ምን ያህል እንደከሰረ የሚያመለክት ነው። ይቺን
ኣጋጣሚ ተጠቅሜ፥ ባለፈው ዓመት እዚህ ከምኖርበት ዴንማርክ ያጋጠምኝን ኣብነታዊ ክስተት ላካፍል።
ኣንዲት Save the Children ብለው ፈረንጆቹ የሚቀልዱበት መያድ/NGO ሰራተኛ የሆነች እህት ካዲስ ኣበባ
ወደዚህ ለስራ ጉዳይ ስትመጣ ጓደኛዋ የሆነች ዘመዴ ኣስቂኙን የበረከት ስምኦን መፅሓፍ (የሁለት ምርጫዎች ወግ) ልካልኝ መፅሓፉን
ለመውሰድ እሆቴሏ ድረስ እሄዳለሁ። ከናይሮቢ መጣሁ የሚለው የዚያው የፈረንጅ ገንዘብ መቃረሚያና መሰልያ መያድ ተቀጣሪ የሆነ
ኣንድ ሰው እቦታው ኣብሯት ይቆየኛል። እኔም መልካም ሰው የሆንቺው እህትና ኣብረዋት የነበረው ግለሰብ በኢትዮጵያ ባህላችን መሰረት
እንግዶቼን ለመጋበዝ ጠየቅኩ። ኣብሯት የነበረው ሰው እኔ ኣብርሃም ያየህ መሆኔን ሲያውቅ ያደረበት ጭንቀት ለመግለፅ ያዳግተኛል።
እኔም ጠበቅ ኣድርጌ ልጋብዛችሁ ስል ከጭንቀቱ ብዛት የተነሳ ሳይደብቅ "ካንተ ጋር መታየት ችግር ያመጣብናልና ይቅርታ ብታደርግልን"
በማለት የቅጩን ሲነግረኝ፥ ትውልዱ ምንኛ እንደወደቀ ለመረዳት ጊዜ ኣልወሰደብኝም። እኔም፥ ምነው የምትኖረው ናይሮቢ ከሆነ ምን
ያስጨንቅሃል? ኣዲስ ኣበባ የምትኖር ቢሆንምኮ ወያነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ኣስፍኛለሁ ስለሚላችሁ ስርዓቱ የምታሸተው ኣየርና
የምትገናኘው ሰው ጭምር ሊመርጥልህ ኣይገባም ኣልኩት። ሆኖም የሰውየን መረን የለቀቀ ጭንቀት በማየትና ልጂቷንም ከሱ ነጥየ ብቻዋን
ከኔ ጋር እንድትሄድ ስላልፈለግሁ እዚያው ተሰነባብተን እኔም ከወጪ ተገላግየ መፅሓፌንና ልጂቱ ያመጣቺልኝ ቆንጆ ስጦታ ተቀብየ
በሰላም ተለያየን። የሰውየውን ስቃይ ግን ለኔ የሞት ሞት ነው። ይሁን እንጂ፥ ጨናቃው ሰውየ በግልፅ ጭንቁን መናገሩ ለኔ ትልቅ
ትምህርት ነው።
ስለዚህ ኣገር በከይሲ ፖለቲካ ሲታመስ ተቀምጠው የሚመለከቱ ሁሉ ከኣገርና ህዝብ ጠላት ተለይተው የሚታዩ ኣይደሉም
ብሎ መደምደም ይቻላል። ይባስ ብሎም ኣንዲት ጠጠር ሳይወረውሩ ተቀምጠው ሲተቹና ሲራገሙ ማየት በእጅጉ ቀፋፊ ትእይንት ነው።
ኣገሪቷ ቆዳዋ እስኪላጥ ድረስ የሚግጧትና ደሟን የሚመጡት እንዚሁ ነቀዞች መሆናቸው ደግም በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ የሚያስብል
ነው። ነገ ወያነ በሌላ ኃይል ሲተካ በድል ኣጥቢያ ኣርበኝነትና በኣሽከርነት ያዙን ልቀቁን የሚሉት እንደነዚህ ያሉ ደካሞች እንደሚሆኑም
በጃንሆይና በደርግ መንግስታት ውድቀት ማግስት ያየነው ሓቅ ነው። እንደነዚህ ላሉ ደካማ ፍጥረቶች የምንለግሰው ምክር ቢኖር፥ ኣገሪቷ
የጋራ ኣገር ስለሆነች ጥቅሟን እንደምትካፈሉ ሁሉ ችግሯንም መካፈል ስላለባችሁ፥ ኣገሪቷ ስትታመስ ሲሆን በግልፅ ኣልያም በድብቅ
በትግሉ መሳተፍ የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን ነው።
ትርጉም የለሹን የሻዕቢያና የወያነ ጦርነት ስለደገፉ ሰዎች
የወያነ ጦርነት የደገፉ ሰዎች በሶስት ረድፍ ከፍሎ ማየት ይቻላል። በመጀመሪያ ረድፍ የተሰለፉት፥ እስከ ግጭቱ ድረስ
ሌላውን ኢትዮጵያዊ እያሳደዱ ከሻዕቢያ ጋር ኣንድ ኣልጋ ላይ ሲዳሩ የነበሩትና በባድመ መወርር መሬትና ሰማይ በላያቸው ላይ የፈረሰ
የመሰላቸው ኣዝማቾቹ የወያነ ኣባላትና፥ የወያነ ኣባላት ባይሆኑኑም የወያነ ቫየረስ ተሸካሚዎች የሆኑ ሰዎች (ሁሉም የትግራይ ተወላጆች)
ናቸው። የነዚሁ ጉዳይ ብዙ ገለፃ የሚያስፈልገው ኣይመስለንም። ምክንያቱም፥ እንዚሁ ሰዎች ጦርነቱን ከመደገፍ በቀር ሌላ ምርጫ
ሊኖራቸው ኣይችልምና፥ በዚሁ እናሰናብታቸዋለን።
በሁለተኛ ረድፍ የሚፈረጁት ደግም የወያነ ቲፎዞዎች ያልነበሩና ኣንዳንዶቹም እስከናካቴው የወያነ ተቃዋሚዎች የነበሩ
ፈረንጆቹ beneficiaries' of crisis የሚሏቸው ናቸው። (የNaomi Klein ድንቅ መፅሓፍ "Shock
Doctrine" ያነበቡ ካሉ፥ በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ ፕሮፌሰሮች በሚሰበከው ጉደኛ ዶክትሪንና ፍልስፍና መሰረት እየተመሩ፥
ያሜሪካ ካፒታሊስቶች ከመሬት መናውጥ፥ ከሱናሚ፥ ከጦርነትና፥ ከሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ኣመጣሽ ምስቅልቅሎች እንዴት ኣርገው
ሃብት እንደሚያግበሰብሱ ይረዱታል።) በዚያው ልክ በዚህ ረድፍ የተሰልፉትም በባድመ crisis ለመጠቀም ሲሉ ውጥረት ላይ ከነበረው
የወያነ ስርዓት ትርፍራፊ ለመለቃቀም ኣሰፍስፈው የሚሯሯጡ ነበሩ።
በሶስተኛው ረድፍ የነበሩት ደግሞ ኮሚኮች ነበሩ። በባድመ ግርግር ከወያነ ጠመንጃ ኣፈፍ ኣርገው ጦርነቱ ሲያበቃ መለስ
ባስታጠቃቸው ጠመንጃ መለስን ለመምታት ያለሙና "ከባድመ መልስ ወደ መለስ" የሚል ኣስቂኝ መፈክር ያነገቡ ነበሩ። ይሁን እንጂ፥
እነዚህ የዋሆች ከባድመ ሲመልሱ ጠመንጃውም ኣልተመረቀላቸውም፥ ጓድ መለስም ቤተመንግስቱን ኣልለቀቀላቸምና በብስጭትና በቁጭት
ሲባዝኑ ይገኛሉ። ሌሎች በዚህ ረድፍ የሚካተቱት ደግሞ፥ መላዋን ኤርትራን ከህግ ውጭ ያስረከበ ወያነ የኢትዮጵያ ድንበርና ሉኣላዊነት
3

ኣስከባሪ ይመስል "ኣገር ተወረረ" በሚልና፤ የኢትዮጵያ ሉኣላዊነት በባድመ ኩርማን መሬት ይለካ መስሏቸው "ሉኣላዊነታችን ተደፈረ"
በሚል ስሜት ልጆቻችንን ወደ ባድመ እንዲተሙ ያደረጉ ቅን ሰዎች ነገር ግን በእጅጉ የዋህ የሆኑ ፍጥረቶች ናቸው።
ያም ሆነ ይህ፥ እነዚህ በሶስቱም ረድፎች የተደረደሩት ሰዎች፥ ዛሬ ላይ ቆም ብለው ትብብራቸው ለኢትዮጵያ ያስገኘው
ጥቅም ሲገመግሙ የሚያገኙት ውጤት የዜሮ ድምር ውጤት መሆኑን ለመረዳት የሮኬት ሳይንቲስት ኣያስፈልጋቸውም። በኣስር ሺዎች
የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎችንና በቢልዮን ብር የሚቆጠር ፍራንክ የባከነላት ባድመና ሌላም ከባድመ ይብልጥ የሚያሳስብ የኢሮብ መሬትና
ህዝብ ዕድሜ ለወያነ በህግ ተረጋግጦ ለኤርትራ ተሰጥቷል። ኃይል ህግን የሚሽር ይመስል ኣሁንም ባድመ የኛ ናት እያሉ የሚያቅራሩ የወያነ
ስርኣት ቲፎዞዎች በቅዠት ዓለም ሰምጠው መቀጠላቸው ግን የሚያስገርመን ኣይደለም።
እንግዲህ፥ እጅና እግራቸውን ኣጣጥፈው የተመለከቱና ወያነን ኣጅበው ትርጉም የለሹን ጦርነት የደገፉት ሰዎች በተመለከተ
ተነጋገርን። ኣሁን የቀረው ጦርነቱን ተቃውመን ሌላ መላምት ይፈለግ ያልነውና ወደ ኤርትራ ያመራነው ሰዎች ጉዳይ ነውና በዚሁ
እንነጋገር።
በኛ ስሌት" ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ የሚደረግ ማንኛውም ግኑኝነት በሁለት አማራጭ ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ ነው።
አንደኛው ምርጫችን፥ እኛም ግማሽ መንገድ ተጉዘን፤ ሻዕቢያም ግማሽ መንገድ መጥቶ መሃል መንገድ ላይ በመገናኘት፥
በማያሻማ መንገድ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለወደፊቱ ማንም ሊነቀንቀው በማይችል ዘላቂ ስምምነት ኣማካኝነት፥ ባስገዳጅ ምክንያት በሁለት
ኣገሮች የሰፈረው ነገር ግን በደም፥ በስጋና ባጥንት ኣንድ ህዝብ የሆነውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በፌደረሽን/ኮንፌደረሽን
ለማስተሳሰር መጣር የሚል ነበር። ይህ እምነታችን ኣሁንም ኣልተለወጠም፤ ኣይለወጥምም።
 ሁለተኛው ምርጫ ደግሞ፥ በኤርትራ በኩል የሚያዳምጠን ሰው ጠፍቶ የመጀመሪያው ሃሳባችን ማስፈፀም የማይቻል
ከሆነ፥ ምንም እንኳ ኣሳዛኝና ቀፋፊ ምርጫ ቢሆንም፥ ከወያኔ ጋር ሆነን ሻዕቢያን ማስወገድና አስመራ ላይ መልካም ጎረቤት ሊሆነን
የሚችል ኣዲስ ስርዓት እንዲመሰረት መርዳት የሚል ነበር። ይህ ኣቋማችን ኣሁንም እንደተጠበቀ ነው።
ስለዚህ፥ በባድመ ግጭት ማግስት በነዚህ ምርጫዎች መካከል ተወጥረን ነበር ስንራወጥ የነበርነው። እግዚኣብሄር ፈቃዱ
ሆኖ፥ የመጀመሪያው ምርጫችን ተስፋ ሰጪ መሆኑን በተጨባጭ ሆኔታ ስለተገነዘብን ደግሞ፥ የማንንም ወሬና ኣሉባልታ ሳያስደነብረን
ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ለመምከር፥ ትርጉም የለሹ ጦርነት የኛ እጅና ድጋፍ የሌለው መሆኑን ለማሳመን፥ በዚያ ክፉ ጊዜ በኤርትራ
ህዝብ መሃል መገኘታችን ኣስፈላጊም ጠቃሚም ስለነበር ያለ ምንም ማወላወል ደፍረን ወደ ኤርትራ ተጓዝን። የመጀመሪያው ምርጫችን
በተጨባጭ ሆኔታ የተገነዘብንበት መንገድ የዚህ ቁልፍ መጣጥፋችን ይዘት ስለሆነ ከታች በዝርዝር የሚቀርብ ይሆናል። ከዚያ በፊት ግን
ኣንዲት ነገር ኣስጨብጠን ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ኣብረን እንጓዛለን።
በርካታ ሰዎች፥ የወያነና የሻዕቢያ ግጭት እንደተከሰተ እኛ ወዲያውኑ ዘለን ወደ ኣስመራ የሄድን ይመስላቸዋል። ይህ ግን
ከግምትና ከጥንቆላ ባለፈ ፈፅሞ ትክክል ኣይደለም። እኛ ወደ ኤርትራ የሄድንበት ትክክለኛ ጊዜ ከግጭቱ በኋላ ሁለት ዙር ጦርነቶች
ተካሄደው፥ ኣብዛኛው ሻዕቢያ ተቆጣጥሮት የነበረውን መሬት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ካስመለሰ በኋላ ነው። ከነዚህ ሁለት ዙር
ጦርነቶች ቀጥሎ ደግሞ ሁለቱም ስርዓቶች በሽምጋዮች ኣማካኝነት ወደ ሰላም ጠረጴዛ ያመራሉ ተብሎ በታመነበትና "ቴክኒካል
ኣረንጅመንት" በመባል የሚታወቀው የሰላም ድርድር ሰነድ ከዛሬ ነገ ይፈራረማሉ በሚባልበት ማለትም ሶስተኛው ዙር ጦርነት ከመጀመሩ
ከሶስት ሳምንታት በፊት ነው። እንዲያውም ወያነ የቀሰቀሰው የሶስተኛው ዙር ጦርነት፥ በኢትዮጵያ እሁድ ምርጫ ሊካሄድ ዓርብ የተጀመረ
ስለሆነ፥ ለዚያ ዙር ጦርነት መቀስቀስ ምክንያቱ የኛ በኤርትራ ምድር መገኘትና የኤርትራ ሚዲያ ተጠቅመን መልእክታችን ለህዝባችን
ማስተላለፍ መጀመራችን ለመሆኑ እኛም ኤርትራውያኑም እናምንበታለን።
ለመንደርደሪያ ያህል፥ ይህንን ካስጨብጠን ዘንዳ ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለሳለን።
በባድመ ግጭት ማግስት
ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር መነጋገርና
ወደ ኤርትራ መሄድ ለምን ኣስፈለገን?

ከኤርትራ መንግስት ጋር ተገናኝቶ መነጋገር እጅግ ወሳኝና ኣስፈላጊ መሆኑን ለማመን የተገደድነው በሶስት ምክንያቶች
ነበር። እነዚሁም፤
4

ኣንደኛ፤ የግጭቱ መነሻ ምክንያት የድንበር ይገባኛል ጥያቄ የቀሰቀሰው ያለመሆኑን ስለምናውቅ ብቻ ሳይሆን ለግጭቱ
መከሰት፥ ዋናዎቹና ወሳኙን ሚና የተጫወቱት ኣገር ቤት ያሉ ቆራጥና ኣስተዋይ ወገኖቻችን ቢሆኑም፥ የኛም እጅ የነበረበት በመኖሩ ሌሎች
የማያውቁት ምስጢር ስለምናውቅና የኛ ፍላጎት ሻዕቢያንና ወያነን ማለያየት እንጂ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለማፋጀት ስላልነበረ
ነው። (ይህንን በተመለከተ በግጭቱ ማግስት ወዲያውኑ "ኣስቸኳይ መግለጫ" በሚል ርእስ ኣገር ቤት ይታተም በነበረው "ጦቢያ"
መፅሄትና፥ በነ ዶ/ር. ጌታቸው ኃይሌና ተባባሪዎቻቸው ባሜሪካ ይታተም በነበረው "ኢትዮፕያን ረጂስተር/Ethiopian
Register" በተሰኙ እውቅ የሚዲያ ውጤቶች ኣማካኝነት ለህዝብ ይፋ ኣድርገናል። በኋላም ባገር ቤት ይታተም በነበረ "ኢትኦጵ"
በተባለ ዝነኛ መፅሄትና፥ በካናዳ/ቶሮንቶ በሚታተመው "ሓዋርያ" ጋዜጣ ኣማካኝነት "የኤርትራ ፋይል ሲከፈት" በሚል ሰፊ ፅሑፍ ውስጥ
ተካቶ ለህዝብ ቀርቧል። እነዚህ የሚዲያ ውጤቶች ለማግኘት ዕድል ያልነበራቸው ዜጎችን ለማስተናገድ ያህልና፥ የግጭቱ ሰበብ በትክክል
መረዳት ወደ ኤርትራ ካስኬደን ምክንያት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ስለሆነ አጠር ባለ መልኩ የዚህ ክፍል ሁለት መጣጥፍ ሶስተኛ ምዕራፍ
ሆኖ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለብቻው ይቀርባል።)
ሁለተኛ፤ ከኢትዮጵያ በገፍ እና በግፍ የተባረሩት ትውልደ ኤርትራ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችና የኤርትራ ዜግነት ያላቸው
ኤርትራዊያን (ቁጥራቸው ከሰማኒያ ሺ በላይ ነው) የተባረሩበት ሆኔታ ኣስጠንተን ባገኘነው መረጃ መሰረት ጉዳዩ የኢትዮጵያንና የኤርትራን
ህዝቦች ዘለቄታዊ ግኑኝነት እንደሚጎዳና የወያነ ስርዓት ይህንን ያደረገበት ምክንያትም በቅጡ ስላወቅን፥ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና
ተግባር ስላልሆነ የምንቃወመው መሆኑንም ለኤርትራ ህዝብና መንግስት በተጭባጭ ማስረዳት አሳፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው። (የወያኔ ስርዓት
ትውልደ ኤርትራ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችና የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ኤርትራዊያን ለማባረር የፈለገበትና በጥናት የደረስንበት ሶስት
ምክንያቶች በሌላ መጥጣፍ እንመለስበታለን።)
ሶስተኛ፤ በኛ በኩል፥ ምንም እንኳ ሁለቱም ስርዓቶች ወደሰላም ጠረጴዛ እንዲሄዱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት
(ተ.መ.ድ.) እና በተለያዩ ኃያላን መንግስታት ግፊት የሚገደዱ መሆናቸውን ብናውቅም፥ ሁለቱም ስርዓቶች ግን ሰላም ኣውርደው ዘላቂ
ግኑኝነት ይፈጥራሉ የሚል ግምት ኣልነበረንም። ኣሁንም የለንም። ስለሆነም፥ በኢትዮጵያ በኩል የወያነ ስርዓት ሊያከናውነው
የማይቻለውን ተግባር፥ ማለትም የሁለቱም ኣገሮች ህዝቦች ሊኖራቸው የሚችል ዘላቂ ግኑኝነት፥ ከኛ በስተቀር ሌላ ሰው ሊሰራው
የማይቻለው መሆኑን በሚገባ ስላሰበመርንበት።
ከዚህ ግምገማ በመነሳት፥ ውስንና ደካማ የነበረውን የመንቀሳቀሻ ኣቅማችን በፈቀደ መጠን በኣካልም ሆነ በስልክና
በኤሌክትሮኒክ መጋናኛ ዘዴዎች ኣማካኝነት መድረስ የቻልናቸውን ኢትዮጵያዊያን የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች ዘንድ ደርሰን ከኤርትራ
መንግስትና ህዝብ ጋር ውይይት እንደምንጀምርና የምንወያይበት ምክንያትና የምንወያይባቸው ነጥቦች በምን ጉዳዮች እንደሚያተኩሩ
በሚገባ ኣስረድተናል። ካነጋገርናቸው ሰዎች ያገኘነው መልስና ኣስተያየትም፥ እነሱ ለጊዜው በግልፅ ለመሳተፍ እንደሚቸግራቸው
ከመስጋታቸው በቀር ባቀረብናቸው ትንተናዎችና ልንወስደው ባቀድነው እርምጃ ላይ ምንም ተቃውሞ የሌላቸው መሆኑን ነው። ከዚህም
ሌላ፥ ሁሉም ያነሱት እንደነበረው፥ እኔ ቀደም ሲል ከሻዕቢያ ጋር ከነበረኝ ጠብና ቅራኔ ኣንፃር ሻዕቢያ በኔ ላይ አደጋ እንዳያደርስ
የነበራቸው ስጋት ነበር የሚገልፁልኝ። በከፍተኛ ጭንቀት ተወጥሮ የነበረው ሻዕቢያ ስራ ፈትቶ ኣብርሃም ያየህ የተባለን ቀንደኛ የወያነ
ጠላት ለማባረር ይባጃል ብለው ያሰቡ ሰዎች፥ በፖለቲካ ዓለም የዘለዓለም ጥቅም እንጂ የዘለዓለም ጠላትም ይሁን የዘለዓለም ወዳጅ
የሚባል ነገር እንደሌለ በውል ያልተረዱ የዋሆች ናቸው።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ፥ ነገሮች መያዣ መጨበጫ እያጡ ሲሄዱ ግን፥ እውቅ ግለሰቦችና፥ የተደራጁ የተቃዋሚ ኃይላት
መሪዎች በኛ ኣማካኝነት በተናጠል ከኤርትራ መንግስት ተወካዮችና ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር እየተገናኙ ተወያይተዋል። ከነዚሁ መካከል
5

ጎላ ጎላ ያሉትን ለመጥቀስ ያህል፤ ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁ1
 ከኢህኣፓ/ኢዴኃቅ፥ እውቁ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ በግል፥ ኢንጂነር
ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ ከኢብኣግ/ENUF2
፥ ኣቶ መልኬ መንግስቴ ከመኣህድ፥ ልጅ ካሳ ከበደ ከኢሰፓና ሌችም ይገኙባቸዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ፥ እኛ ከማንም ሳንደበቅና በግልፅ መንገድ ከኤርትራ መንግስት ወኪሎች ጋር ግኑኝነት መፍጠር
የጀመርነው ከጄኔቭ ከተማ ነበር። የመጀመሪያው ግኑኝነት ጄኔቭ የሆነበት ምክንያት ባንድ ጉዞ ሁለት ነገሮችን ለማከናወን ነበር።
ባንድ በኩል፥ በወቅቱ ጄኔቭ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) 55ኛ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ዓመታዊ
ጉባኤ የሚካሄድበት ጊዜ ስለነበረ፥ ከላይ እንደጠቀስነው፥ ከኢትዮጵያ በገፍ እና በግፍ የተባረሩት ትውልደ ኤርትራ ኢትዮጵያዊያን
ወገኖቻችና የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ኤርትራዊያን ጉዳይ ኣስመልክተን በዚያ መድረክ የወያነውን እርኩስ ድርጊት በይፋ በማውገዝ የታሪክ
ማስረጃ ለማስመዝገብ ነበር። በዚሁ መሰረት The African Association of Education for Development የተባለ ድርጅት
ባደረገልን መልካም ትብብር በተ.መ.ድ. መድረክ ዕድል ኣግኝተን በኢትዮጵያ ስም ድርጊቱን ኣወገዝን ግጭቱ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ
የመንግስታቱ ማህበር ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርግ ተማፅኖኣችን ኣስተጋባን።3

(እኔንም እንደ ዘመዴ መለስ ዜናዊ ሞት ሳይቀድመኝ እዚችው ደግ ሰዎችን እንድመርቅ ይፈቀድልኝ። የኤርትራዊያኑ
በግፍ መባረር በረጅሙ ላገራችን ጦስ የሚያስከትል መሆኑን በውል ተረድተው ስፖንሰር ያደረግንን ድርጅት በማስተዋወቅና ጄኔቫ
በቆየንበት ጊዜና በሌላም ጊዜ በገንዘብና በሞራል ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉልን ድንቅየ ኣገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ክቡር ኣቶ ተረፈ
ራስወርቅንና ክብርት ባለቤታቸው ወ/ሮ. ብርሃኔ ኣስፋውን በዚች ኣጋጣሚ ከልብ ልናመሰግናቸውና በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ ፊት
ልንመሰክርላቸው ይገባናል። ምስኪኑ ያማራ ህዝባችን ካሉት እጅግ በጣም ጥቂት ኣኩሪና ተቆርቋሪ ኣገር ወዳድ ምሁራን ልጆቹ መካከል
እነዚሁ ሁለት ዜጎቻችን በግምባር የሚጠቀሱ ናቸው ብንል ማጋነን ኣይሆንብንም። ከዚህ በተጨማሪ፥ ሌላው ብርቅየ ጀግና የኢትዮጵያ
ልጅ ክቡር ፕሮፌሰር ኣስራት ወልደየስ፥ ቢያንስ በእስር ቤት እንዳይሞቱና ከእስር ተፈተው ህክምና ወደሚያገኙበት ኣገር እንዲሄዱ፥ ክቡር
ኣቶ ተረፈ ራስወርቅ ከኛ ጋር ሆነው የተጫወቱት ሚና እና ይህንን በማድረጋቸው የተገኘው ውጤት በታሪክ ማህደራችን መዘግበን
ያሰፈርነው ሃቅ ነው። እግዚኣብሔር ውለታችሁን ይክፈል!)
ሌላው ጄኔቭን የጉዳያችን ማስፈንጠሪያ ቦታ ኣድርገን የመረጥንበት ምክንያት በዚያ ጉባኤ የኤርትራ የልኡካን ቡድን
እንደሚገኝ የታወቀ ስለሆነ የኤርትራ መንግስት ተወካዮችን ኣግኝተን ስለ እቅዳችን ልናወያያቸው እንችላለን በሚል እምነት ነበር።
እንዳሰብነውም፥ እኔ ወረቀቴን በጉባኤው መድረክ ላይ ኣንብቤ እንደጨረስኩና ለእረፍት ኣዳራሹን ለቅቄ ስወጣ ከኤርትራ የመጣው
የኤርትራው ልኡካን መሪ ኣምባሳደር ኣማረ ተክሌና የስራ ባልደረቦቹ ቀድመው ካዳራሹ ወጥተው ኖሮ ከበር ቀልበው በየተራ አቅፈው
ሳሙኝ። ቀጥሎም ከልኡካኑ ጋር ኣብረን ባዳራሹ ውስጥ ከሚገኘው ካፌ ሄደን ቡና ይዘን መነጋገርን ጀመርን።
ኣምባሳደር ኣማረ በንግግራችን መክፈቻ የተናገረው ነገር እስካሁን ድረስ በጀሮየ ያቃጭላል። "ዛሬ የሰራኸው ስራ
በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች ዘንድ ለዘለዓለም የማይረሳና፥ ወያኔ የገነባውን ኣሳፋሪ የጥላቻ ግንብ ብትንትን ኣድርገህ ያፈራረስክበት
ታላቅ ስራ በመሆኑ ልትኮራ ይገባሃል። በዚህ የተቀደሰ ስራህ በኤርትራ ህዝብና መንግስት ስም እናመሰግንሃለን።" የሚል ነበር። እውነት
ለመናገር ያምባሳደሩን ቃላት ስሰማና ያምባሳደሩ የሰውነት እንቅስቃሴ ቋንቋ (body language) ስመለከት የተሰማኝን ደስታ
በቃላት ለመግለፅ ይቸግረኛል። ምክንያቱም የነዚህ ኤርትራዊያን በግፍ መባረር በዘሌቀታው ባጠቃላይ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ
መካከል፥ በተለይ ደግሞ በትግራይና በኤርትራ ህዝብ መካከል፥ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ አደገኛ ስለነበር ይህንኑ ለመስበር መቻላችን ለኛ

1
 በወቅቱ ባሜሪካ የኤርትራ ኣምባሳደር የነበረውን ኣቶ ሰመረ ርእሶምንና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ልዩ ኣማካሪና የፖለቲካ ጉዳይ
ኃላፊ የሆነው ኣቶ የማነ ገብረኣብን በኣካል ኣግኝቶ ያነጋገረው ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁ ብቻ ቢሆንም፥ ሌሎች ሁለት ከፍተኛ የኢህኣፓ ኣመራሮች ማለትም
ኣቶ ፋሲካ በለጠና ኣቶ ተገኝ ሞገስም ስለ ግኑኝነቱ የሚያውቁ ሲሆን፤ እኔንና ኣቶ ኢያሱን ወደ መጀመሪያው ዙር መገናኛ ስፍራ/ሆቴልና ወደ ሁለተኛው
ዙር ስብሰባ ወደ ኤርትራው ኣምባሳደር መኖሪያ ቤት በመኪና ያደረሱንም ሁለቱ ነበሩ። ይህንን ግኑኝነትና፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ (ዩጋንዳ በነበርኩበት ጊዜ)
እኔና ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁ (ኣቶ ኢያሱ ኢዴኃቅን በመወከል) ሁለት ጊዜ ወደ ዝምባብዌ ተጉዘን ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያምን መጎብኘታችንና
በዚሁ ግኑኝነት ኣምካኝነት ከደቡብ ሱዳኑ ዶ/ር. ጆን ጋራንግ ዴማብዮር ጋር ስለመገናኘታችን ሌሎች የኢህኣፓና የኢዴኃቅ ኣመራሮች እውቅና የሰጡት
ይሁኑ ኣይሁኑ ምንም የማውቀው ነገር የለም። ለማወቅ ግን እጓጓለሁ።
2
 http://www.enufforethiopia.net/Documents/AboutENUF.html
3
 http://www.un.org/News/Press/docs/1999/19990409.hrcn906.html
6

ከሁሉም የበለጠ ስራ ነበርና። በዚህ ኣጋጣሚ ይህንን እኩይ ተግባር በይፋ ወጥተው የኮነኑት (እንደኛ የተ.መ.ድ. ዓይነት ደማቅ መድረክ
ለማግኘት ኣጋጣሚውን ባያገኙም) ታላቁ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ብቻ ነበሩ። ከዚህ በተረፈ፥ ይህንን የመሰለ ኣደገኛ
ድርጊት በመፈፀሙ ሌላ ሰው ሲኮንን ኣልየሁም፤ ኣልሰማሁም። የ"ባጣ ቆየኝ" ፖለቲከኞቻችን (የግንቦት ሰባት ሰዎችን ጨምሮ) ዛሬ
እያስተናገዳቸው ያለውን ደግ የኤርትራ ህዝብ እንደዚህ ያለ ኣሰቃቂ ግፍ በላዩ ላይ ሲፈፀምበት ምን ብለው ነበር? ብለን ኣንጠይቅም።
(እዚቺም፥ ሞት ሳይቀድመኝ ኣንድ ወገኔን ልመርቅ። በዚያ ፈታኝ ወቅት፥ የኛ ዓላማ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በመረዳት
ከጎናችን ያልተለየንና በኛ ላይ ከተሰነዘረው የነ ባጣ ቆየኞቹና የወያኔ ቲፎዞዎች የደንቆሮ ጦር የገሸለጠው፥ በተ.መ.ድ. ይሰራ የነበረና የጄኔቫ
ኗሪ የሆነው፥ በደግነቱና ባገር ወዳድነቱ የሚደነቅ ብልህ ወገናችን ኣቶ ክፍሌ ተካን ይህንን ኣጋጣሚ ተጠቅመን ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን
ልናቀርብለት እንወዳለን። እግዚኣብሄር ዋጋህን ይክፈልልን!)
(በኣንፃሩ ደግሞ፥ ኣሁንም ይህንን ኣጋጣሚ ተጠቅሜ፥ ለትግራይና ለኣማራ ተወላጆች የወያነ ቲፎዞዎች (በተለይ ጄነቫ
የሚኖሩትን) ኣንዲት ነገር ወርውሬላቸው ወደ ቁምነገሬ ልመለስ። የኤርትራውያኑ በግፍ መባረር በመኮነናችን፥ የትግራይ ተወላጆች የወያኔ
ቲፎዞዎችና የወያኔ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካና ትግል ምንም ስፍራ የሌላቸው ኣልኩባዮች "ለምን ኤርትራዊያን
ተባረሩ ብላችሁ ትጮሃላችሁ" በሚል ቡራ ከረዩ ሲሉ ከርመው ነበር። ጊዜ መስተዋት ነውና፥ ለነዚህ ነቀዞች ኣሁን በምንገኝበት መድረክ
ላይ ሆነን የምናቀርብላቸው ፈታኝ ጥያቄ ኣለን። "እንደሚታወቀው፥ ሟቹ ጌታችሁ መለስ ዜናዊ (ኣፈሩን ያቅልልለትና) ኤርትራዊያኑ
መባረራቸው ኣግባብ ያለመኖሩን ኣምኖ ደግሞ ደጋግሞ ንስሃ መግባቱን ኣይታችኋል። ንስሃ መግባት ብቻ ሳይሆን የተባረሩት ኤርትራዊያን
ተመልሰው ንብረታቸውን እንዲሰበስቡ (ንብረቱን በልታችሁ የጨረሳችሁት ቢሆንም) በምኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ መመሪያ
ኣውጥቶላቸዋል። እናም፥ እኛ ስንለው ኩነኔ የሚሆነው፥ ጌቶቻችሁ ሲሉት ግን ፅድቅ የሚሆነው ለምን ይመስላችኋል?" ብለን እንጠቃለን።
መልሳችሁን ግን ኣንጠብቅም። የምንጠብቀው የፍርድ ቀን ነው። የፍርዱ ቀን እንደሚመጣ ደግሞ ቅንጣት ታክል ኣትጠራጠሩ ብለናችሁ
ወደ ቁምነገራችን እንመለሳለን።)
መልካም ኣጋጣሚ ሆኖ፥ ኣምባሳደር ኣማረ የታላላቆቼ ታላቅ የሆነው የሟቹ ወንድሜ ያቶ ኣሰፋ ያየህ (ሰማይ ነብሱን
ይማረው) የተማሪ ቤት (ጄኔራል ዊንጌት) ጓደኛው በመሆኑና የኛን ቤተሰብ ማንነት በሚገባ ስለሚያውቅ ለኔ ተጨማሪ ዕድል ነበር።
የኣምባሳደር ኣማረ መልካም ንግግርና ምስጋና በደስታ ከተቀበልኩ በኋላ፥ ከነበርንበት ግቢ ወጣ ብለን ልናነጋራቸው እንድምንፈግ
ነገርኩት። ኣምባሳደር ኣማረም ቦታ እንድንመርጥ ዕድሉን ለኛ ሰጠን። እኔም ኤምባሲያችሁ ውስጥ ቢሆን ይመረጣል ስላልኩት ተያይዘን
በሱ መኪና ወደ ኤምባሲው ሄድን።
ከኤምባሲው እንደደረስን ውይይቱን እኔ መጀመር ስላለብኝ "ከዚህስ ወዴት?" በሚል ጀመርኩ። ከዚያ በመቀጠል፥ በኛ
በኩል የተወሰደውን ኣቋም ምን እንደሆነ ኣስረድተን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ባስቸኳይ ሁነኛ ሰዎች መድቦ እንዲያነጋግሩንና ዝርዝር ጉዳዮች
ከፕሬዚዳንቱ ዘንድ ለሚላኩት ሰዎች የምናቀርብ መሆኑን ኣስረዳሁ። ኣምባሳደር ኣማረም ባስቸኳይ ካስመራ ጋር ተነጋግሮ
እንደሚያስታውቀኝ ኣስረድቶኝ በዚሁ ተለያየን።
ከዚያ በኋላ ጀኔቫ ከመልቀቀቻን በፊት ኣምሳደር ኣማረ ካስመራ ጋር ተነጋግሮ የፕሬዚዳንቱ ቢሮ ከሁለት ሳምንት
በዚያው በጄኔቭ ሰው እንደሚመድብና ከዚያ ሰው ጋር በሚደረስ ስምምነት ዋናውን ውይይት የሚጀመርበት ጊዜና ቦታ እንድንወስን
መስማማቱን ነግሮኝ በዚሁ ተስማማን።
በኛ በኩል፥ ይህ ወሳኝ የሆነ የመጀመሪያ ኦፊሰኤላዊ ግንኙነት፥ በትግራይ ሰዎች ብቻ ማስጀመር መልካም ስላልመሰለን
ቢያንስ ለጄነቫ ቅርብ ከሆነ ያውሮጳ ኣገር ኣንድ የትግራይ ተወላጅ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሰው እንዲሳተፍ ኣስፈላጊ መሆኑን
ኣመንበት። ስለሆነም፥ በጉዳዩ ላይ እናወያያቸው ከነበሩና የፖለቲካ ብስለት ካላቸው እውቅ ሰዎች ኣንዱ ፓሪስ የሚኖረው የኤህኣፓ የበላይ
ኣመራር ኣባል የሆነውን ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁን መጋበዝ እንደሚመረጥ ኣመንበት። ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁን የመረጥንበት ምክንያት የኢህኣፓ
የበላይ ኣመራር በመሆኑ ብቻ ኣይደለም። ኣቶ ኢያሱ ቀደም ሲል (ኡጋንዳ በነበርኩበት ጊዜ) ብዙ ድርጅቶች ያቀፈውን "የኢትዮጵያ
ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት፤ (ኢዴኃቅ)" ወክሎ ለኣምስት ዓመታት ያክል ኣብረን ብዙ ስራዎች የሰራን ስለነበረ፥ የሱ በስብሰባው
መገኘት ኢህኣፓን ብቻ ሳይሆን በኤዴኃቅ ስር የተጠቃለሉት ኃይሎችንም ጭምር ይወክላል ከሚል ግንዛቤ ነው። በመሆኑም ኣቶ ኢያሱ
ዘንድ ደውየ ስለ ውሳኔያችን ኣስረዳሁትና እሱም በሃሳቡ ተስማምቶበት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ጄኔቭ ላይ እንድንገናኝ ተስማማን።
ከሁለት ሳምንታት በኋላ እኔና ኣቶ ኢያሱ ጀኔቫ ላይ በኤርትራ ኤምባሲ ጽ/ቤት ውስጥ በኤርትራው ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት
በኩል ከተመደበው ከኣምባሳደር ዓንደብርሃን [ዓምደብርሃን] ወልደጊዮርጊስ ጋር ተገናኘን። (ኣምባሳደር ዓንደብርሃን መቀመጫውን
ብራስለስ/ቤልጄም ኣድርጎ፥ በወቅቱ ለቤኔሉክስ፥ ለኣውሮጳ ህብረት፥ ለፈረንሳይ፥ ለፖርቱጋል፥ ለስፔይን፥ ለእንግሊዝና ለዩኔስኮ የተወከለ
የኤርትራ ባለሙሉ ስልጣን ኣምባሳደር ነበር።) ከፕሬዚዳንቱ ልኡክ ኣምባሳደር ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ ኣጠቃላይ ሃሳባችን ገልፀን፥
7

በተለይ ያሰመርንበት ነገር፥ ግጭቱ በድንበር ሳቢያ የተከሰተ ያለመሆኑንና ክሁሉም በላይ በኤርትራ በኩል መወሰድ ያለበት እርምጃ
የቀረበውን የሰላም መፍትሄ ሃሳብ ባስቸኳይ መቀበል መሆኑን፥ ቀጣይ ውይይቶቻችንም ውጤት የሚኖራቸው ይህ ሲደረግ መሆኑን
ማስታወሻ አስያዝን። ሌላው ግልፅ ያደረግነው ጉዳይ፥ የኛ ዓላማ ከባድመ ወዝግብ ባሻገር የሚያሳስበን በዘለቄታው የኢትዮጵያና የኤርትራ
ህዝቦች ከሰመጡበት ማጥ ወጥተው እንዴት ተቃቅፈው በሰላም ሊኖሩ ይችላሉ? የሚለውን ጥያቄ በተጨባጭ መልስ እንዲያገኝ ማድረግ
እንደሆነ፥ እንደዚህ ያለ ሰፊ ጉዳይ ደግሞ ባንድ ስብሰባ የሚቋጭ ስላልሆነ፥ በኤርትራ በኩል ኣንድ ቋሚ ልኡክ ተመድቦ የሚቀጥለው
ስብሰባ ብዙ ኢትዮጵያዊኖች በሚገኙበት በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ ሆኖ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ መወያየት ኣስፈልጊ መሆኑን ኣስረዳን።
ኣምባሳደሩም እዚያው እያለን ከሌላ ክፍል ሄዶ ወደ ኣስመራ ደውሎ ሲመለስ ከሶስት ሳምንታት በኋላ ዋሺንግተን ተገናኝተን ስራችንን
መጀመር እንደሚቻል ኣስታወቀን። እኛም በዚሁ ቀነቀጠሮ ተስማምተን ወደየመጣንበት ተመስስን።
ይህንን ቀነቀጠሮ ከመድረሱ ከሁለት ሳምንት በፊት እኔ ብቻየን ወደ ዋሺንግተን በረርኩ። ይህንን ያደረግኩበት በሁለት
ምክንያቶች ነበር።
ኣንደኛ፤ ከላይ እንደጠቀስኩት ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁ በዚህ ወሳኝ ስብሰባ በመገኘቱ በኢዴኃቅ ስር የተሰባሰቡትን ወሳኝ
የፖለቲካ ኃይሎችን ይወክላል ብለን ኣምነናል። ይሁን እንጂ፥ በግል የኔ የቅርብ ወዳጆች የሆኑ እንደነ ኣቶ ማሞ ወልዱ (ኣሁን ጀርመን ኣገር
የሚኖርና ካሁን በፊት ኣኩሪ ስራ የሰራ) ያሉ ጠቃሚ ሰዎች የታቀፉበትና በእውቁ ኢትዮጵያዊ በኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የሚመራውን መድህን
ፓርቲ እንዲሳተፍ ማድረግ ኣስፈላጊ ነው ብለን ኣመንበት። መድህን ፓርቲ ቀደም ሲል የኢዴኃቅ ኣባል የነበረ ሲሆን እኛ ኡጋንዳ
በነበርንበት ጊዜ ራሱን ከኢዴኃቅ ያገለለ (በግሌ በማውቀው ኣሳማኝ ምክንያት) ቢሆንም፥ በወቅቱ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ድርጅት ስለነበረ
ፓርቲው በዚህ ስብሰባ እንዲገኝ ማድረግ ገንቢና ምክንያታዊ ነበር። ስለሆነም፥ ኣብዛኛዎቹ የመድህን ፓርቲ ዋና መሪዎች መቀመጫቸው
ዋሺንግተን ዲሲ ስለሆነ የስብሰባው ቀን ከመድረሱ በፊት እነሱን ኣግኝቼ እንዲቀላቀሉን ለማድረግ ፈለግሁ። በዚሁ መሰረት ባደረግሁት
ጥረት ከመድህን ፓርቲ ከፍተኛ ኣመራር ኣባላት መካከል ሶስት ሰዎች ካረፍኩበት ሆቴል ተገናኝተን ስለሆኔታው ኣስረዳሁ። እነሱም ልጅ
ሰይፉ ዘውዴ (የልዑል ኣልጋወራሽ ኣስፋወሰን ኃ.ሥ. ልጅ ባለቤት)፥ ኣቶ ደጀኔ ኣያሌውና፥ አሁን ስማቸውን የረሳሁት የቀድሞ የመከላከያ
ኃይላችን ኣባልና የበላይ መኮንን የነበሩ (የሻለቃ ወይም የኮሎኔል መኣርግ ያላቸው ይመስለኛል) ነበሩ። ሶስቱም ሰዎች ሃሳቤን በሚገባ
ኣዳምጠው ሲያበቁ ከፓርቲያቸው ጋር እንደሚወያዩበትና ውጤቱን እንደሚያሳውቁኝ ኣስረድተውኝ ተለያየን። ሆኖም ከዚያ በኋላ
ኣልደወሉልኝም። ቀድሞውንም እነሱን ማግለል ኣያስፈልግም ከሚል እሳቤ እንጂ በስብሰባው ተሳተፉም ኣልተሳተፉ የሚያመጣው ለውጥ
ኣልነበረምና ብዙ ኣልተጨነቅኩበትም።
ሁለተኛ፤ የኤርትራው መንግስት ዋና ልኡክ ካስመራ ከመምጣቱ በፊት የቅርብ ወዳጄና በውቅቱ ባሜሪካ የኤርትራ
ኣምባሳደር የነበረው (ባሁኑ ጊዜ የኤርትራ የትምህርት ምኒስትር የሆነው) ኣምባሳደር ሰመረ ርእሶምን በግል ኣግኝቼ ከዋናው ስብሰባችን
በፊት ኣንዳንድ ነገሮች ላማክረው ፈልገሁ። ኣምባሳደር ሰመረ ርእሶም በትግሉ ዘመን ሱዳን በነበርኩበት ጊዜ በሱዳን የህዝባዊ ግምባር
(ሻዕቢያ) ተጠሪ ሆኖ ሲያገለግል በቅርብ የምንተዋወቅና፥ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ፥ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱንም በቀ. ኃ. ሥ. ዩኒቨርሲቲ
ያጠናቀቀ ስለሆነ ስለ ኢትዮጵያ በቂ እውቀት ያለው ሰው ከመሆኑ ባሻገር ትሑትና ቅን ኤርትራዊ ዜጋ በመሆኑ ለኔ ቁልፍ ሰው ነው። ከዚህ
ግንዛቤ በመነሳት፥ ከዋናው ስብሰባ በፊት በግል ኣግኝቼ ኣንዳንድ ነገሮች ባጫውተው ይጠቅማል የሚል የሚል እምነት ኣሳደርኩ። በዚሁ
ምክንያት ኣምባሰደር ርእሶም ዘንድ ደውየ ዋሺንግተን መድረሴና ከስብሰባው በፊት ላገኘው እንደምፈልግ ጠይቄው በደስታ ተስማምቶ
ካንድ የስራ ባልደረባው (ስሙን ኣልያዝኩትም) ጋር ሆኖ በነጋታው በዋሺንግተን ሬናይሳንስ ሆቴል ተገናኘን።
በዚህ የግል ስብሰባ ላይ ከወዳጄ ከኣምባሳደር ሰመረ ከስራ ባልደረባው ጋር ብዙ ነገሮች ኣንስተን ተጨዋወትን። በበኩሌ
ያነሳሁባቸው ነገሮች ጀኔቫ ላይ ለኣምባሳደር ዓንደብርሃን ካነሳንለት ጉዳዮች የተለየ ኣልነበረም። በጄኔቫ ቴክኒካዊ ስብሰባ ያልተነሳና፥
በዋናው ስብሰባ ላይ ላነሳው የተዘጋጀሁበት ኣንድ ጠቃሚ ጉዳይ ለወዳጄ ለኣምባሳደር ርእሶም በማንሳት ስሜቱን ለመረዳት የፈለግሁበት
ልዩ ጉዳይ ግን ነበረኝ። ይኸውም፤ ቀደም ሲል ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኣፈወርቂ ካሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ያማርኛው ኣገልግሎት ጋር ኣንድ ቁልፍ
ቃለ መጠይቅ ባደረገ ጊዜ፥ "ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌደራሲዮን መተሳሰር ይገባቸዋል" ሲል የተናገረው ቃል መሰረት በማድረግ በዋናው
ስብሰባችን ላይ ብናነሳው ምን ይመስልሃል? የሚል ነበር። (የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ቃለ መጠይቅ ቃል በቃል ከታች ኣቀርበዋለሁ።)
የወንድሜና ወዳጄ ያምባሳደር ሰመረ መልስ ኣጭርና ቀጥ ያለ የማያወላውል መልስ ነበር። ባጭሩ ያለው ለመጥቀስ
ያህል፥ "ይህ ምን ችግር ኣለው! ያነሳኸው ሃሳብ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ባጋጣሚ ጥያቄ ቀርቦለት ባጭሩ ይህንን ማለቱ ሊያስገርምህ ኣይገባም።
የኢትዮጵያና የኤርትራ የወደፊት ዘላቂ ግኑኝነት ከዚህም በላይ እንዲሆን የኤርትራ ህዝብና መንግስት ቋሚና የማይናወጥ ኣቋም ብቻ
ሳይሆን በፖሊሲ የተያዘ ኣጀንዳ እንደሆነ ላረጋግጥልህ እፈልጋለሁ። እኔ ከምነግርህ በላይ ግን፥ ካስመራ የሚመጡት ልኡካን በበለጠ
ሊያስረዱህ ስለሚችሉ ሳታመነታ ጉዳዩን ልታነሳውና ከዚያም ኣልፈህ ልትጠይቅ የምትችል መሆኑን ልገልጽልህ እወዳለሁ።" የሚል ነበር።
እውነት ለመናገር የሰማሁት ነገር በውኔ የሰማሁት ሳይሆን ህልም ነበር የመሰለኝ። ያም ሆነ ይህ፥ ይህንን ከሙዚቃ በላይ የሚጣፍጠው
የወዳጄ ልቤ የወንድሜ የኣቶ ርእሶም መልስ ሰንቄ ወዳጄ የገዛልኝን ቡና ጨልጨ ተሳስመን ወደየሰፈራችን ተመለስን።
8

ይህንን ካልኩ በኋላ፥ ልባችን እስኪወልቅ ድረስ ለምንታገልለት ህዝባችና ላንባቢዎች በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያህል፥
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ካሜሪካ ድምፅ ሪዲዩ ጋር ያደረገው ታሪካዊ ቃለ መጠይቅ (ለወደፊቱ VOA ወይም ኢሳት/ESAT ከማህደሮቻቸው
ኣፈላልገው በድምፅ እንደሚያቀርቡልን ተስፋ እያደረግሁ) እኔ ወደ ፅሑፍ የመነዘርኩትን፥ ኣንዲት ቃል ሳልጨምር ወይም ሳልቀንስ፥
እንዳለች እዚቺው ለማቅረብ ይፈቀድልኝ።
ኣቶ ኢሳያስ ኣፈወርቂ
ከኣሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ ያማርኛው ክፍል
ከጋዜጠኛ ኣዳነች ፍስሃየ ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ

ጋዜጠኛ ኣዲሱ ኣበበ፥ እየተገባደደ የነበረውን የኣውሮጳውያን የ1992 ዓ.ም. ምክንያት በማድረግ በተገባደደው ዓመት
ከተከስቱ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹን ሲያስተናግድ፤ "1993 ዓ.ም. ላይ ደርሰናል፤ እንደ ኣውሮጳ ኣቆጣጠር። ኣቶ ኢሳያስ ኣፈወርቂ ስለ
ኤርትራ ሬፈረንደም፥ ማለትም ህዝበ ውሳኔ፥ ይህን ብለው ነበር።" በሚል መክፈቻ የስራ ባልደረባው የሆነቺው ጋዜጠኛ ኣዳነች ፍስሃየ
ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኣፈወርቂ ጋር ቀደም ሲል በድምፅ ያደረገችውን ቃለመጠይቅ ይለቃል።
ጋዜጠኛ ኣዳነች ፍስሃየ፤
በግዴታም ይሁን በውዴታ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ተሳስስራ ቆይታለች። እና፥ እንግዲህ፥ የነፃነት ጥያቄ፥ የመገንጠል
ጥያቄ ከማን? የሚለው [መልሱ] ከኢትዮጵያ ነው። እንግዲህ፥ [ኤርትራ] ከኢትዮጵያ ጋር ተሳስራ ስለቆየች። እና፥ ይህ የሬፈረንደሙ ነጥብ
ራሱ ምንድንነው የሚለው፤ "ነፃነት ትፈልጋለህ? ኣዎን ወይም ኣይደለም" ዓይነት ነው። እና፥ ለምንድነው እንደዛ የጠበበው? ትንሽ ሰፋ ብሎ
ወይም ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ኣንድነት ወይም ኮንፌደረሽን ወይም ፌደረሽን ወይም ሰፋ ያለ የራስ ገዝ ኣስተዳደር ወይንስ ነፃነት ነው
የምትመርጠው? በሚል ሰፋ ባለ ይዘት ለምን ኣልቀረበም?
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፤
በመጀመሪያ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እየተገነጠለች ነው የሚለውን ጥያቄ እኛ በበኩላችን ከመጀመሪያውም
ኣልተቀበልነውም። የምንቀበለው ነገርም ኣይደለም። በኛ ኣስተያየት ጥያቄው ምንደንነው? ህጋዊ ያልሆነ ጋብቻ ወደ ፍች በሚያመራበት
ወቅት ወደ ህግ መልሶ ለማረጋገጥ የሚቻል ኣይመስለኝም። የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ስለመዋሃዱ ጉዳይ በህጋዊ መንገድ የተደረገ
ኣልነበረም። ስለዚህ ለኤርትራዊያን የሚቀርበው ጥያቄ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ትፈልጋለህ? ወይንም ኣትፈልግም? የሚል ሳይሆን፥ ነፃ ኣገር
እንድትሆን ትፈልጋለህ? ኣትፈልግም? የሚለው መሆኑ ባህሪያዊ የሆነ ነገር ይመስለኛል። ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ትጠላዋለህ፥
ኣትወደውም፥ ከኢትዮጵያ ጋር ዝምድና የለህም፥ ኣይኖርህምም ማለት ኣይደለም።
ጋዜጠኛ ኣዳነች ፍስሃየ፤
ያኔ፥ ጋዜጣዊ መግለጫ በተደረገበት ጊዜ፥ የኤርትራ ህዝብ ወይም መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የኤኮኖሚ ውህደት ወይም
ኢንቲግሬሽን እንደሚፈልግ፥ ከዛም ኣልፎ እንዳውም እስከ በኮንፌደርሽን የመዋሃድ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ጠቅሰው ነበረ። እና ይህ
ኣባባል ምን ያህል እውነትነት ኣለው? ምን ያህልስ የሚገፋበት ነገር ይመስለዎታል?
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፤
ከዚያም በኋላ ደጋግሜ እንደገለፅኩት ሁሉ፥ ጥያቄው ስለቀረበ፥ ለረጅም ጊዜ በቆየው ኣመለካከታችን መሰረት
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለያድግ ስለሚችል ዝምድና በሚመለከት ጭንቅላታችን ምን ጊዜም ቢሆን ክፍት ነው። በኤርትራና
በኢትዮጵያ መካከል ሊኖር ስለሚችል ማንኛውም ዓይነት ገንቢ መረዳዳት ገደብ የሚደረግበት ነገር ኣይሆንም። በኮንፌደረሽን መዋሃድ
የሚፈለግ ከሆነ፥ ለምን ኣይሆንም እንላለን። መንግስታት ፈለጉት ኣልፈለጉት በኤርትራና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ለወደፊት ትውልዶች
የሚቀጥል የመዋሃድ ዝምድና መኖር ኣለበት። በፍላጎትና በምኞት ላይ ብቻ ሳንወሰን በተጨባጭ ወደ መዋሃድ ወደሚያመሩን እቅዶች
መግባት ኣለብን። እንዲህ ሲባልም ምንልባት ኣንዳንዶቹ፥ እነዚህ ችጋራሞች የሚበላና የሚጠጣ ስለሌላቸው ሊጠቀሙብን ፈልገው ነው
ኣሁን ውህደት የሚሉት፤ ለጥቅማቸው ሲሉ ነው፤ ይሉ ይሆናል። ይህ ግን ገንቢ ኣይሆንም።" (የቃለመጠይቁ ጥቅስ መጨረሻ።
ሰረዝ/ኣፅናኦት የኔ።)

 (የኔ ኣስተያየት፤ ኣፈሩን ያቅልልለትና፥ መለስ ዜናዊ እና ግብረኣበሮቹ በኤርትራ ዙሪያ ድብቅ ዓላማ ባይኖራቸው ኖሮ፥
ይህንን ያቶ ኢሳያስ ሃሳብ ቀልበው ሻዕቢያን ወደ ጠረጴዛ ጋብዘው በቀላሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በፌደራላዊ ትስስር ሊዋሃዱ
ይችሉ እንደነበር ለመገመት ኣያስቸግርም። ብሎም ትርጉም ከሌለው ጦርነት ገብተን ከመተላለቅና ከመማቀቅ ለመዳን እንችል ነበር።)
ወደ ፍሬነገሩ ለመመለስ፥ ጄኔቫ ላይ ላነጋገረን ኣምባሳደር ዓንደብርሃን እንደገለፅንለት ሁሉ፥ የሰላም መፍትሄ ሃሳቡን
ባፋጣኝ እንዲቀበሉ ለኣምባሳደር ሰመረም ኣጥብቄ ኣስታውሼው ነበር። ኣምባሳደር ዓንደብርሃን እንደነገረን፥ የኤርትራ መንግስት የራሱን
የቤት ስራ ለማጠናቀቅ ሲል ከመዘግየቱ በቀር፥ ወያነ እንደሚያናፍሰው ሳይሆን፥ የሰላም መፍትሄው በኤርትራ በኩል ፍፁም ኣማራጭ
የሌለው መሆኑን እንደሚታመንበትና በቅርብ ጊዜ ስምምነቱ ይፋ እንደሚደረግ ገልፆልን ነበር። ይህን በነገረን ከሁለት ሳምንታት በኋላ
9

ሰያጨቃጭቅ የነበረው የሰላም መፍትሄ ሃሳብ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ማግኘቱን ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ከመሆኑ በፊት ኣምባሳደር
ሰመረ ርእሶም በፋክስ ልኮልኝ ወረቀቱ ሲደርሰኝ በጣም ተደሰትኩ።
በተባበሩት መንስታትና ባፍሪካ ህብረት ኣማካኝነት ቀርቦ የነበረውና፥ በኤርትራው ወገን ስምምነት ባለማግኘቱ ለተወሰነ
ጊዜ ተጓቶ የነበረው የሰላም መፍትሄ ሃሳብ እልባት እንዲያገኝ በኛ በኩል የፈለግንበት ምክንያት ከሰላማዊ መፍትሄ ተብየው የሚገኝ
ቁምነገር ኖሮ ሳይሆን፥ ምናልባት የኛና የኤርትራ መንግስት ወይይት ተሳክቶ ወደ ኤርትራ እንድንጓዝ ኣስፈልጊ ሆኖ ቢገኝ ሁለቱም ኣገሮች
በጦርነት ላይ እያሉ ወደ ኤርትራ መሄዱን ስላልፈለግነው ነበር።
እንግዲህ፥ በእንደዚህ ያለ ሆኔታ ላይ እያለን ነበር ከኤርትራ መንግስት የሚላኩትን ልኡካን በመጠባበቅ ላይ የነበርነው።
እኔ ቀደም ብየ ዋሺንግተን መድረሴ ከላይ የገልፅኩ ሲሆን ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁም የስብሰባው ቀን ከመድረሱ ከጥቂት ቀናት በፊት
ዋሺንግተን ደረሰ። ይሁን እንጂ በኤርትራው ወገን የሚመጣው የልኡካን ቡድን በወቅቱ በነበረው የስራ ድርብርቦሽ ምክንያት ከተባለው
ጊዜ ትንሽ ዘግይቶ ዋሺንግተን ደረሰ። ልኡካኑ ዋሺንግተን ዲሲ እንደረሱ ከሶስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ እንድንገናኝ ተወስኖ በተቆረጠው ቀን
ከዋሺንግተን ከተማ ትንሽ ወጣ ብሎ በሜሪላንድ ክፍለሃገር ከሚገኝ ኣንድ Holiday Inn ከተባለ ሆቴል ብዙ የጓጓንለት ስብሰባ
እውን ሆነ። በስብሰባው ላይ በኛ በኩል እኔና ኣቶ ኢያሱ ዓለማየሁ ስንገኝ፥ በኤርትራው ወገን የተገኘው ልኡክ የተመራው ደግሞ
ኣምባሳደር ሰመረ ርእሶምን ጨምሮ በኤርትራው ፕሬዚዳንት የቅርብ ረዳትና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ኣመራር የፖለቲካው ክፍል ኃላፊ
በሆነው በኣቶ የማነ ገብረኣብ ነበር።
ለዚህ ግኑኝነትና ስብሰባ ምክንያቶቹ እኛ ስለነበርን፥ ውይይቱ የተከፈተውም በኛ በኩል ነበር። እኛ የሰነዘርነው ሃሳብ
ባጭሩ የሚከከተሉትን ነጥቦች ያካተተ ነበር።
· ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታየው የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ሁለገብ ግኑኝነት እጅግ የተዛባ የነበረ ከመሆኑም በላይ፥
ግኑኝነቱ የሁለቱ ድርጅቶች (የወያነና የሻዕቢያ) ግንኙነት እንጂ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ወይም ሚዛኑን የጠበቀ የሁለቱ ኣገሮች
ግንኙነት ያልነበረ መሆኑን፤
· ኤርትራና ኢትዮጵያ ኣንድ ላይ ተሳስረው የነበሩ እንደመሆኑ መጠን በድንበሮች ኣካባቢ በትክክል ተከልሎና ባለቤትነቱ የማን
እንደሆነ በሚገባ ተለይቶ ያልታወቀ መሬት ሊኖር ይችል ይሆናል የሚል ግምት ቢኖረንም ቅሉ፥ ኣሁን የተነሳው ግጭት ግን
በምንም መንገድ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ያልተከሰተ መሆኑን ጠንቅቀን የምናውቅ መሆኑን፤
· በተዛባው ግኑኝነትና በነ መለስ ዜናዊ ሁለገብ ትብብር በትግራይ ህዝብ ስም ኤርትራ ነፃነቷን የተቀዳጀችበት ሆኔታ በሌሎች
ኢትዮጵያዊያን በኩል የትግራይ ህዝብን ለኣደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን፤
· የትግራይ ህዝብ ሊደርስበት ከሚችል ኣደጋ ለመከላከል ሲባል ብቻ፥ የተወሰኑ ንቁ ልጆቹ ሆኔታዎች ኣስገድዷቸውና የተዛባውን
የኢትዮጵያና የኤርትራ ግኑኝነት ለመስበር ሲሉ ላለፉት ኣምስት ዓመታት ያህል ህቡእ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩ መሆኑን፤
· የተዛባውን ግኑኝነት ለመስበር ሲባል የተደረገው ትግል ምንም እንኳ ሻዕቢያንና ወያኔን ለማለያየት በተተለመለት እቅድ መሰረት
የተሳካ ውጤት ኣስገኝቷኣል ለማለት ቢቻልም፥ በሁለቱም መንግስታት ኣማካኝነት በሚወሰዱ ኣላስፈላጊ እርምጃዎች4
 ከታቀደለት
ዒላማ ውጭ ሄዶ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ወገኑ ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ያለውን ዘላቂ
ግኑኝነት ሊጎዳ በሚችል ሆኔታ ላይ የወደቀ መሆኑን፤
· ኣሁን የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ከወያነ ጋር መደራደር ዘላቂ መፍትሄ የማያስገኝ መሆኑን፥ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት
የሚቻለው ከወያነ ውጭ ካሉት ኃይሎችና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመቀራረብ ብቻ መሆኑን፥ የወያነ ስርዓት ቢትዮጵያ የህዝብ
ድጋፍ ስለሌለው ወያነ የሚስማማበት ማንኛውም መፍትሄና ውሳኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፤
· ማንኛውም የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ከጦርነት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት ያለበት መሆኑን፤

4
 ለምሳሌ ያህል፥ ኣስመራንና መቀሌ/ዓይደርን በኣውሮፕላን ቦንብ መደብደብ ከሚጠቀሱ ኣላስፈጊና ኣደገኛ እርምጃዎች ናቸው።
በነገራችን ላይ፥ ዓይደርን የደበደበው ኣብራሪ/ፓይለት ኤርትራዊ ሳይሆን ወያነ የሻዕቢያን ኣብራሪዎች እንዲያሰለጥለት ለሻዕቢያ የለገሰው የደርግ ኮሎኔል
ፓይለት የነበረ የኣማራ ብሄር ተወላጅ ነው። ስለ ዓይደር ኣሳዛኝ ድብደባ ዝርዝር ታሪክ ጊዜ ሲተርፈን የምንነጋርበት ሲሆን፥ ደብዳቢው ኣብራሪ ግን
ሻዕቢያ በቁጥጥር ስር ኣቆይቶ ኢትዮጵያ ነፃ ፍርድ ቤቶች ስታቆም ተከሳሹም መብቱ ተጠብቆና በሚገባ ተከላክሎ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ እንዲደረግ
በጠየቅነው መሰረት ኣብራሪው ከኤርትራ መሬት እንዳይወጣ ታግዶ በጥበቃ ስር ይገኛል። ኤርትራ ሄደን ከሰራናቸው ቁልፍ ስራዎች ውስጥ የትግራይ
ህዝብ ማደራጀታችን/ማስታጠቃችን (ለኢትዮጵያ ጥቅም ሲባል) እና የዓይደር ሰማእታትን ገዳይ ማን እንደሆነ በሚገባ ኣውቀን እርምጃ ማስወሰዳችን
ነው ብለን እናምናለን።
10

· የኤርትራን ነፃነት ያረጋገጠው ሬፈረንደም በማንኛውም ረገድ ህጋዊና ትክክለኛ ኣግባብ ተከትሎ የተካሄደ ካለመሆኑ ባሻገር፥
የኢትዮጵያን ህዝብ የወከለ ፓርላማና መንግስት ባልነበረበት ሆኔታ የተካሄደ በመሆኑ፥ ምንም እንኳ በኛ በኩል የኤርትራን ህዝብ
ውሳኔ በህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እስከተፈፀመ ድረስ ተቃውሞ የሌለን ቢሆንም፥ የተካሄደው ሬፈረንደምና ውቴቱ ግን
ህጋዊ ነበር ብለን የማናምን መሆኑን፤
· በተባበሩት መንግስታት ውሳኔና ዋስትና መሰረት ኢትዮጵያም ተስማምታበት የቆመውና፥ በቀድሞ መሪያችን በቀ. ኃይለ ሥላሴ
የፈረሰው የኢትዮጵያና የኤርትራ ፌደረሽን በኤርትራ ህዝብ ውሳኔና ፈቃድ ያላገኘ መሆኑን የምናምን ሲሆን በዚሁ ሰበብ የፈሰሰው
የህዝብ ደምና የወደመው ንብረት ኣሳዛኝና መኮነን ያለበት መሆኑንም እየተገነዘብን፥ ለሁለቱም ህዝቦች ዘላቂና ኣስተማማኝ ሰላም፥
ብልፅግና፥ ዋስትናና ጥንካሬ የሚያስገኝ፥ ባካባቢያችንም መረጋጋት የሚሰያሰፍነው ኢትዮጵያና ኤርትራ ኣላግባብ የፈረሰውን
ፌደረሽን በበለጠና ባስተማማኝ መንገድ በፅኑ መሰረት ላይ ኣቁመው ኣብረው ሲኖሩ ብቻ ነው የሚል ፅኑ እምነት ያለን መሆኑን፤
· ሻዕቢያና ወያነ ሰምና ወርቅ በነበሩበት ወቅት ወያነ በኦሮሞ ነፃነት ግምባርና በመሰል ድርጅቶች ላይ የፈፀመው ግፍ የኤርትራ
መንግስት በተጨባጭ የሚያውቀው ቢሆንም፥ በወቅቱ ሻዕቢያ ትኩረት ያልሰጣቸው እነዚህ ኃይሎች ኣሁን ከወያነ ጋር
በተጋጨበት ማግስት ማቅረቡ ኣጠያያቂ መሆኑን፥ ከዚህም የተነሳ ከህብረተሰባችን በኩል የተወሰነው ክፍል ሻዕቢያ ከነዚህ የብሄር
ድርጅቶች ጋር ብቻ ግኑኝነት መፍጠሩ ኢትዮጵያን ለመበተን ካለው ዕቅድ ነው የሚል ስጋት ያለው መሆኑን፥ ሆኖም በኛ በኩል
በተፈጠረው ግኑኝነት ላይ ተቃውሞ ባይኖረንም በተናጠል በሚደረግ ትግል ፈጣንና ኣስተማማኝ ውጤት ይገኛል ብለን
የማናምን መሆኑን፥ በበኩላችን ከትግራይና ከኣማራው ክፍል በመለስ የሚኖረውን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝባችን ችግር ጠንቅቀን
የምናውቀውና ችግሩንም ለመቅረፍ ከነዚሁ ወገኖች ጋር ተቀራርበን በመስራት ላይ መሆናችንን፥ ስለሆነም በፅኑ እምነት ተነሳስተን
ከነዚህ ወገኖቻችን ጋር ከምናደርገው መቀራረብ ኣኳያ የኤርትራ መንግስትና ህዝብም ከጎናችን ቆሞ ትብብር እንዲያደርግ ኣስፈላጊ
መሆኑን።
እንግዲህ፥ እኛ ትኩረት ሰጥተን ያነሳናቸው ሃሳቦች ጠቅለል ባለ መልኩ ከላይ የተመለከቱት ነበሩ። እነዚህ ሃሳቦች ሰፊና
ጥልቅ ውይይት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ስለምንረዳ፥ ከኤርትራው መንግስት ልኡካን ጋር የተራዘመ ውይይት ይኖረናል የሚል ግምትም
ነበረን። ይሁን እንጂ፥ በሚያስደንቅ ሆኔታና ከጠበቅነው ውጪ፥ የኤርትራው ልኡክ መሪ ኣቶ የማነ ገብረኣብ ፈፅመን ሰምተነው የማናውቅ
ኣስገራሚ የሆነ ነገር ኣመጣልን። ኣቶ የማነ ገብረኣብ ነገር ዓለሙን ያሳጠረው እንዲህ በማለት ነበረ።
· ወያነ እንደሚለፍፈውና ብዙ ሰው እንደሚያስበው የግጭቱ ዋነኛ መንስኤ የመሬት ጉዳይ እንዳልሆነ በቂ ግንዛቤ ኣለን፥ የግጭቱ
ብቸኛ መፍትሄም በጦር ሜዳ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ የሚገኝና በኤርትራ መንግስት በኩልም ይህንን በተመለከተ ግልፅ
ኣቋም ኣለ።

· የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በጋራ ሲኖር የሚኖረው ጥቅምና ጥንካሬ እጅግ የላቀ መሆኑን የምናምንበት ከመሆኑም በላይ፥ የኛ
በጋራ መኖርና ጠንክሮ መውጣት ጠቀሜታው ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ኃይል ሆነን በኣፍሪካ ቀንድ
የሚታየውን ቀውስ ከማስወገድ ባሻገር ባጠቃላይ በመላው ኣፍሪካ ያለውን ቀውስ ለመቅረፍ የሚያስችል ሆኔታ መፍጠር
እንደሚቻል መንግስታችን ጠንቅቆ ያውቃል።

· የኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ምን እንደሆነ በውል እንረዳለን። ኣሁን የምንኖርባት ዓለም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በግሎባል
ኤኮኖሚ ምክንያት ወደ ትንሽ ገጠርነት በተቀየረችበት ክፍለለ ዘመን የትናንሽ ኣገሮች ፖለቲካዊ ነፃነት መረጋገጥ ብቻውን
የተሟላ ነፃነት እንደማያረጋጥም እንረዳለን። ከዚህና ከኬሎች ብዙ ወቅታዊና ታሪካዊ ምክንያቶች በመነሳት የኢትዮጵያና
የኤርትራ ህዝብ ኣንድነት ከራሳችን ኣልፎ ለኣካባቢያችንና ለመላው ኣፍሪካ የሚሰጠውን ጠቀሜታ በውል በመገንዘብ
የኢትዮጵያና የኤርትራ ፌደራላዊ ኣስተዳደር እንድንመሰርት ያለንን ፍላጎት ቀደም ኣድርገን ለወያነ መንግስት ኣቅርበናል። የወያነ
መንግስት በማናውቀው ምክንያት ሃሳባችንን ካለመቀበሉም ሌላ ይህንን ሃሳብ ካቀረብንበት ጊዜ ኣንስቶ በሁለቱም ኣገሮች
ለነበረው መልካም ግኑኝነት ሳንካ ለመፍጠር እንደተንቀሳቀሰ ኣስተውለናል። ለወደፊትም ቢሆን ስርዓት በተከተለና ኣግባብ
ባለው መንገድ ከህዝባችን ጋር መክረን በህዝባችን ፍላጎትና ውሳኔ ተመስርተን ይህንኑ ሃሳብ የምናራምድ መሆናችንን
ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

· በብሄር ከተደራጁ ድርጅቶች ብቻ ግንኙነት ታደርጋላችሁ ለተባለው ቅስቀሳው የወያነ ቅስቀሳ ከመሆኑ ባሻገር ትክክለኛ መረጃ
ኣይደለም። እኛ የምናደርገው ግንኙነት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብና በብሄርም ሆነ በህብረ-ብሄራት ከተደራጁ ድርጅቶች ጋር
እንደሆነ ለማንም ግልፅ ሊሆንለት ይገባል። ከዚህ ውጭ ኣንተ በብሄር ኣንተ ደግሞ በህብረ-ብሄር ተደራጅ እያልን መመሪያ
የመስጠት መብት የለንም። ድርጅቶች በህብረት እንዲሰሩ ለማድረግ ሙሉ ፍላጎታችን ቢሆንም እጅ ኣየጠመዘዝን ድርጅቶችን
እንዲያብሩ ማድረግ ግን በድርጅቶቹ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ከመሆኑም በላይ ስራው የኢትዮጵያዊያኖች እንጂ የኛ ሊሆን
11

ኣይገባም። የኛ ዕቅድና ፍላጎት ኢትዮጵያን ለመበተን ቢሆን ኖሮ በደርግ ውድቀት ማግስት ልናደርገው እንችል ነበር።
የተበታታነች ኢትዮጵያ ደግሞ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለኛም ጠንቅ እንድምትሆን ኣጠያያቂ ኣይደለም። እኛ ግን በተቃራኒው
በሽግግሩ ጊዜ በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዲሰፍን ያበረከትነው ኣስተዋፅኦ ወዳጅም ጠላትም በሚገባ ያውቀዋል። በኢትዮጵያ
መበታተን የኤርትራ ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል ብሎ የሚያስብ ካለ የታመመ ሰው ብቻ መሆን ኣለበት። ስለዚህ ወያነ ለራሱ
ህልውና ሲል የሚለፍፈውን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከመሆን በመታቀብ ታጋይ ኢትዮጵያዊያንና ባጠቃልዩም የኢትዮጵያ
ህዝብ የኤርትራ ችግር የተከሰተበትን ምክንያትና ለሰላሳ ዓመታት ያህል የተካሄደው ትግል ምንነት በማጤን ሁላችንም
ከስህተቶቻችን ተምረን ስህተቶች እንዳይደገሙ በውይይትና በመግባባት ህዝባችንን ለተሻለ ህይወት ለማብቃት ከመታገል ሌላ
ኣማራጭ የሌለን መሆኑን ጠንቅቀን ማወቅ ይገባናል።

· በኢትዮጵያ ውስጥ ኣሳሳቢ ችግር ያለ መሆኑን እንገነዘባለን። ችግሩን በሚገባ ተረድቶ ዘላቂ መፍትሄ መሻት ደግሞ የሁላችን
ተሳትፎ እንደሚጠይቅ እናምንበታለን። ኣሁን የገባንበት የኢትዮጵያና የኤርትራ ችግር በኣንድ ተጨባጭ ፎርሙላ ማስተካከል
ከተቻለ ደግሞ ሌላው የውስጥ ችግር ህይወት ኖሮት ሊቀጥል ስለማይችል ወዲያውኑ እንደሚፈታ ለመገንዘብ ኣስቸጋሪ
ኣይደለም። ስለሆነም ችግሩ በተናጠል የኢትዮጵያ የውስጥ ችግር ተብሎ የሚቀርብ ሳይሆን የጋራ ችግር መሆኑን ተረድተን
መፍትሄውን በጋራ ለማስገኘት በኤርትራ መንግስትና ህዝብ በኩል ይህ ቀረው የማይባል ትብብር እንዳለና ለወደፊቱም በዚሁ
እንደሚቀጥል ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

እንግዲህ ከኤርትራው የልኡካን ቡድን የተሰጠን መለስ ይህንን የመሰለ ነበር። በኛ በኩል ይህንን ሁሉ የምንሰማው ካንድ
ከፍተኛ የኤርትራ መንግስት ባለስልጣን መሆኑን ለማመን እስከመጠርጠር ደርሰን ነበር ማለት ይቻላል። የሰማነው ሁሉ ሁሉ ልባችንን
ሰልቦ ከሰመጥንበት የሃሳብ ውቅያኖስ ወጥተን ትንሽ ነፍስ ዘርተን ከተነፈስን በኋላ፥ ሶስት ጥያቂዎች ኣቀረብን። እነዚሁም፡-
1. በመጀመሪያ ከኤርትራ በኩል የቀረበውን የፌደረሽን ሃሳብ የወያነ ስርዓት ኣልቀበልም ሲል ያቀረባቸው ምክንያቶች ምን ነበሩ?
2. የኤርትራ መንግስት ይህንን ሃሳብ ለወያነ ማቅረቡንና እነ መለስ ዜናዊ ሃሳቡን ወድቅ ለማድረጋቸው በኤርትራው ወገን በወቅቱ
ለኢትዮጵያ ህዝብ ለምን ይፋ ኣልተደረገም?
3. ይህ ጠቃሚና ገንቢ የፌደረሽን ሃሳብ ከኤርትራ በኩል ለመቅረቡና የወያኔ ስርዓት ኣልቀበልም ለማለቱ ምን ማረጋገጫ ኣለ?
የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ።
የኤርትራው ልኡክ ለነዚህ ሶስት ጥያቄዎቻችን የሰጠው መልስ በቅደም ተከተል እናቀርባቸዋለን።
1. ኣዲሱ ሃሳብ ሲቀርብም ሆነ ከዚያ በፊት፥ ኣሁን በስራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ በሁለት ነጥቦች ላይ
እርማት እንደሚያስፈልገው በኤርትራ ወገን ለወያነ ስርዓት ሃሳብ ቀርቦ ነበር። እርማቱን በማስመልከት ያቀረብነው ሃሳብ
ኣንዱ የህገ መንግስቱ ኣንቀፅ 39 ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኣፍሪካ ከዚያም ባሻገር ላሉ ኣገሮች ጠንቅ የሚያስከትል
ስለሆነ ሊታረም ይገባል የሚል ነው። ሌላው ነጥብ ደግሞ ፌደራላዊ ኣስተዳደር እንደ ኢትዮጵያ ላለ ኣገር ጠቃሚ ኣማራጭ
መሆኑ መረዳት ቢቻልም፥ ቋንቋን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ኣወቃቀር ግን አደገኛ ስለሆነ መታረም ኣለበት
የሚል ነው። ስለዚህ የወያነ ስርዓት የኛን የፌደራሲዮን ሃሳብ ያጣጣለበት ምክንያት በዋናነት በህገ መንግስቱ ላይ ካለን የተለየ
ኣቋም የመነጨ ነው ብለን እናምናለን።

2. የኛ ሃሳብ በወያነ ተቀባይነት ማጣቱ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ ያለማድረጋችን ትክክል ኣልነበረም። ነገር ግን ይህንን
ያላደረግንበት ምክንያት ነበረን። እንደሚታወቀው በሁለቱም ኣገሮች የነበረው ዘርፈብዙ ግኑኝነት በዚህ ምክንያት እንድሻክር
ባለመፈለጋችንና በሂደት በሁለቱ ኣገሮችና ህዝቦች በኩል ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ኣግኝቶ ተግባራዊ ይደረጋል የሚል እምነት
ነበረን። በወያነ በኩል የተለወጠ ኣመለካከት ሳይኖር ስንሰጋበት የነበረ ማለትም የሁለቱ ኣገሮች ግኑኝነት መሻከር በወያነ
ፍላጎት ተመስርቶ ሊከሰት ቻለ።

3. በኛ በኩል የፈደረሽኑ ሃሳብ ለማቅረባችንና በወያነ ስርዓት በኩል ደግሞ ሃሳቡ ተቀባይነት ላለማግኘቱ በቂ ማስረጃ አለን።
በእንግሊዝኛ we are on record፤ ሲል ኣቶ የማነ ገብረኣብ ደመደመ።
(ሶስተኛውን ጥያቄ እንዲያው ለነገሩ ጠየቅን እንጂ፥ ሌላ ማስርጃ ሳያስፈልገው ከላይ ያስቀመጥነውና ኣቶ ኢሳያስ ኣፈወርቂ
ከኣሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ጋር ያደረገው ቃለመጠይቅ በራሱ በቂ ማስረጃ ነው። ሆኖም ኤርትራዊያኖቹ we are on
record ሲሉ ሌላ ማስረጃም ኣለን ባዮች ናቸው።)
12

ይህንን ቁርጥ ያለ የኤርትራ ባለስልጣን መልስ ማዳመጥ ያሳደረብን ስሜትና ቁጭት ምን ያህል እንደሆነ ኣንባቢ
ይስተዋል ብለን ኣንገምትም። ያም ሆነ ይህ፥ በዚህ ኣስገራሚ ግኝት ስብሰባችን ከተጠናቀቀ በኋላ ከኛ በኩል የተሰነዘረው ሃሳብ ኣጭር
ነበር። ይኸውም፥ የልኡካን ቡድኑን ኣመስግነን፥ የኤርትራ ህዝብ አደገኛ በሆነ ሆኔታ በሚገኝበት በዚህ ፈታኝ ወቅት እኛ ራሳችን በኣካል
ወደ ኤርትራ ተጉዘን በኤርትራ ህዝብ መሃል መገኘት እንደምንፈልግና፥ ማንኛውንም ዋጋ ከፍለንና ታግለን በደምና በታሪክ ወንድማማች
የሆነውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በማያዳግም ሆኔታ ተቃቅፈው እንዲኖሩ ለማድረግ ይህ ቀረው የማይባል ጥረት እንደምናደርግና
ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ መሳካት ደግሞ ህዝባችንን በቀላሉ ማሳመን እንችላለን በሚል ማሳረጊያ ሃሳባችን ደመደምን።
በቃ! ይህንን ስብሰባ በተካሄደ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ኤርትራ ለመግባት የደፈርነው ይህንን መልካም ግኝት
በመጨበጥና መሰረት በማድረግ እንጂ "የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው" በሚል የሞተ ፈሊጥና በሻዕቢያ ጠመንጃ የወያነ ስርዓት እንጥላለን
በሚል ኣልነበረም።
ይህንን መጣጥፍ እዚህ አያቆምም። በሚቀጥለው ሳምንት በምንለቀው የዚህ ክፍል ቀጣይና ኣካል በሆነው "ምዕራፍ
ሁለት" ላይ፥ የኤርትራ መንግስት ይህንን የመሰለ የፌደረሽን ሃሳብ ኣቅርቦ እያለ መለስ ዜናዊ ሃሳቡን ውድቅ ያደረገበት ምክንያት
በህወሓትና በራሱ በመለስ ታሪክ ተመርኩዝን ዝርዝር ትንተና እናሰጣለን። ከዚህ በተጨማሪ፥ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያና የኤርትራ
ህዝብ በፌደራሲዮን እንዲተሳሰሩ ፍላጎት ያለው መሆኑን የሚያሳምኑ ሌሎች ጭብጦች በዚያው ምዕራፍ ይፋ እናደርጋለን።
ይህንን ካልን በኋላ፥ ይህንን ምዕራፍ ኣብቅተን ከመሰናበታችን በፊት ለወገኖቻችን ለግንቦት ሰባት ኣመራሮች
የምናስተላልፈው ጠቃሚ መልእክት ኣለን።
ወንድም ዶ/ር ብርሃኑ፥ የማከብራቸው ደግ ወዳጄና ኣባቴ ያቶ ነጋ ቦንገር ልጅ በመሆኑ የማከብረው ሰው ነው። ዶ/ር.
ብርሃኑ ላያውቀኝ ይችል ይሆናል። እኔ ግን ብርሃኑን በሚገባ የማውቀው ወገኔ ነው። የሜጋ ቀለም ፋብሪካ የሂሳብ ክፍል ኃላፊ
በነበርኩባቸው ሰባት ዓመታት፥ ባንድ ቀበሌ (ቀበሌ 54) ከዶ/ር ብርሃኑ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ኣቅራቢያ (ከሳዶሊን ቀለም ፋብሪካ ኣጠገብ)
በመኖሬ፥ የቀበሌያችን የመጀመሪያው ዙር ተመራጭ በመኖሬ ብርሃኑ በኢህኣፓነቱ ጥቃት እንዳይደርስበት የተከላከልኩለት ስለሆነ (ያባቱ
ውለታ ስላለብኝና ወንድሜ ሙሉ ያየህም የነብርሃኑ ኢህኣፓ ጀሌ በመኖሩ)፥ ዶ/ር. ብርሃኑ የተማረበት ትምህርት ቤት (ንፋስ ስልክ
ኣጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የቦርድ ኣባል በመኖሬና በቦርዱ ስብሰባዎች ላይ የብርሃኑ ጉዳይ በተደጋጋሚ እየተናሳ እንነጋገርበት
ስለነበረ፥ ያባቱ ያቶ ነጋ ንብረት የዳማ ሆቴል ኣስተዳዳሪና ያቶ ነጋ ዘመድ የሆነው ያቶ ኣርጋው ቅርብ ጓደኛ በመኖሬና በሌሎች ብዙ
ምክንያቶች ብርሃኑን ጠንቅቄ የማውቀው ሰው ነው። ይህንን እዚህ ለመጥቀስ የፈልግሁት፥ ያ በወጣትነቱ ዘመን ጠንቅቄ የማውቀው
የብርሃኑ ችኩልነት፥ የ"ገስጥ" ጉራና ግትርነት ኣሁን ብርሃኑ ዶክተር በሆነበት ጊዜም ቢሆን ምንም ያልተለወጠ መሆኑን እያየሁ ስለሆነ
ነው። ይህ ማለት፥ ትምህርት ማለቂያና ማቆሚያ የለሌው ጉዳይ ቢሆንም፥ ብርሃኑ እስኪበቃውና ፀጉሩ እስኪላጥ ድረስ የፈረንጅ ትምህርት
ቢማርም የወጣትነቱ ባህሪ ግን ከቦታው ምንም ኣልተነቃነቀም ማለቴ ነው። የፈረንጅ ትምህርት ጠቃሚ መሆኑ ኣጠያያቂ አይደለም።
በፈረንጅ ትምህርት ቤትና በፈረንጅ ፕሮፌሰሮች ጭንቅላት ወስጥ ግን ብዙ ረቂቅ ምስጢር፥ ታሪክና፥ ውስብስብ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያችን
ኣትገኝም። የኢትዮጵያን ምስጢር የሚያውቁት የኛ ኣያቶች ኣባቶችና እናቶች ነበሩ። እነሱም በኛ ትውልድ ችኩልነትና ኣጉል ኣጉራ ዘለልነት
ተፈጅተው ኣልቀዋል። ጥቂት የቀሩ ኣዛውንቶች ካሉም በዘመናዊያን የሃበሻ ፈረንጆች ሁካታና ጫጫታ መድረኩ ተይዞባቸው እጅና
እግራቸው ታስሮ በኣግራሞት በየቤታቸው ተቀምጠው ኣሎሄ ኣሎሄ በማለትና፥ "እመብርሃን ምነው ኢትዮጵያን ረሳሻት?" በማለት
ፈጣሪያቸውን ሲማጠኑ ይገኛሉ።
የብርሃኑ ብቃትና ታታሪነት ግን አደንቃለሁ። ሆኖም ከፍተኛ ትምህርት መማር መታደልና ወሳኝ ቢሆንም፥ ትምህርት
በራሱ ብቻ ግን በቂ ኣይደለም። ከትምህርት በላይ የሚያስፈልግ ነገር ጥበብ (wisdom) የሚሉት ነገር ኣለ። ከኤርትራ ጉዳይ በተያያዘ
ምሁራን ነን ብለው የሚኮፈሱት የሃበሻ ፈረንጆች ሲደናቆሩ ኣስተውየ፥ ካሁን በፊት በኢትኦጵ መፅሄትና በሓዋሪያ ጋዜጣ ላይ
ካቀረብኳቸው በርካታና ዘርፈ ብዙ መጣጥፎች ባንዱ ላይ፥ በእውቀትና በጥበብ መካከል ያለውን ኣንድነትና ልዩነት ኣስመልክቼ
ናይሮቢ/ኬንያ የሚኖሩ ኣንድ ፓስተር ወዳጄ የነገሩኝን መጥቀሴ ኣስታውሳለሁ። የሁለቱ ሚድያዎች ኣዘጋጆች ወዳጆቼ ጋዜጠኛ ሲሳይ ኣጌና
እና ጋዜጠኛ ሙሉቀን መለሰም ያስታውሱት ይሆናል ብየ ኣምናለሁ። ፓስተሩ ወዳጄ በምሳሌ የነገሩኝን ባጭሩ ለመጥቀስ ያህል፥
"በመፅሓፍ ቅዱስ ወስጥ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሓንስ ራዕይ ያለውን ድንቅ ስራ በሙሉ ብታውቅና ብትተንትን ኣዋቂ ሰው
ልትባል ትችል ይሆናል። ነገር ግን በሱ ብቻ ጥበበኛ ልትሆን ኣትችልም። ጥበበኛ የምትሆነው ከዚያ ታላቅ መፅሓፍ ያገኘኽውን እውቀት
በተግባር በራስህ ላይ ስትፈፅመውና በዚያ መርህ ተወስነህ ስትኖር ነው" በማለት ኣስተማሩኝ።
ፓስተሩ ወዳጄ ትክክል ናቸው። ለኣብነት ያህል፥ ዛሬ በስደትም ይሁን ባገር ቤት ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶክሳዊት ታሪካዊት
ቤተክርስቲያናችንን እንመራለን የሚሉ የሃይማኖታችን ማፈሪያ የሆኑት ጳጳሳትና ካህናት መፅሓፍ ቅዱስን ኣንጠርጥረው የሚተነትኑና ነጋ
ጠባ "ጠላታችሁን ውደዱ" እያሉ በመስበክ የሚባጁ ናቸው። ሆኖም ያ ትምህርታቸውና ስብከታቸው ግን በራሳቸው ላይ ሲፈፅሙት
13

ኣይታዩም። የሚታየው እርስ በርሳቸው ሲቦጫጨቁና ህዝበ ክርስቲያኑን ሲያተራምሱ ብቻ ነው። እናም እንበግናለን። የነሱ ልጆችና
ተማሪዎች የሆኑትና የኢትዮጵያን ህዝብ ባህልና ወግ በፈረንጅ እብደት የተኩ ፍጥረቶች ደግሞ መለስ ዜናዊ የተባለ ፍጥረት እግዜሩ በጥበቡ
ሲወስደው ጀሮ የሚሰነጥቅ ድምፅ ማጉያና ከበሮ ኣንግተው በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ቆመው ሲጨፍሩና ሲያውኩ እያዩ ሊቃነ ጳጳሳቱና
ዲያቆናቶቻቸው ተዉ ኣትባልጉ፥ የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ፥ የሃይማኖታችን ህግና ወግ፥ የሃገራችን ብሂልና ፈሊጥ ይህንን ብልግና
ኣያስተምርም ኣይፈቅድም ብለው ኣያስተምሩም ወይም ኣይገስፁም። ምክንያቱም ለእውቀት እንጂ ለጥበብ ኣልታደሉም። ጥዋት ማታ
የሚደግሙት ታላቁ ቅዱስ መፅሓፍም ቢሆን "የጥበብ መጀመሪያ እግዚኣብሔር መፍራት ነው" ይላል እንጂ "የእውቀት መጀመሪያ" ብሎ
ኣይጀምርምና ጥበብ ስላልታደሉ ጳጳሳቱና ካህናቶቻቸው እግዚኣብሔርን ለመፍራታቸውም እርግጠኞች ኣይደለንም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፥ ታላቁ ኣሜሪካዊ ምሁርና የሃይማኖት መሪ ዶ/ር. ሮበርት ኤች ሹለር "Success is
Never Ending [and] Failure is Never Final" በተሰኘ ውብ መፅሓፋቸው በገፅ 48 ላይ፤ (እጠቅሳለሁ)
"Education is the acquisition of knowledge. As important as it is, knowledge
cannot take the place of wisdom. Recognize that formal education may or
may not be a solid basis for responsible self-confidence. If academic degrees
have increased knowledge but have diminished wisdom, then formal
education have diminished wisdom, then formal education has become
counterproductive." በማለት የእውቀትንና የጥበበን ምንነት በትክክል ይገልፁታል።
ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ፥ ባሁኑ ጊዜ ዶ/ር ብርሃኑ የሚመራው ግንቦት ሰባት የሚጓዝበት ያለው መንገድ
በእውቀትና በገንዘብ ላይ የተመስረተ እንጂ ጥበብ በተላበሰ መንገድ እየተጓዘ ነው ብለን ኣናምንም። ዶ/ር ብርሃኑ ካሁን በፊት፥ "የነፃነት ጎህ
ሲቀድ" በተሰኘው ዳጎስ ያለ መፅሓፉ5
 ላይ የትጥቅ ትግል ብላችሁ ኣታንሱ ባይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በስቶክሆልም/ስዊድን በተጠራ
ኣንድ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ዶ/ር ብርሃኑ ባደረገው ንግግር፥ "ወያነ ጠመንጃ ስለሚያውቅበት በሱ ኣንመጣንበትም። እኛ የምንመጣው ወያነ
በማያውቅበት በሰላማዊ የትግል ስልት ነው" ሲል ኣስተምሯል። ታዲያ! ኣሁን የወያነ የጠመንጃ እውቀት ከሰመ? ወይስ ከምርጫ-97 ወዲህ
የወያነ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤቶች የመርካቶ እንቁላል ማከማቻ ሆኑ ወይስ ባዶኣቸውን ቀሩ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ለነ ዶ/ር ብርሃኑ
ግልጽ ይመስለናል። እናም፥ "ሲያቃጥል በማንኪያ፤ ሲቀዘቅዝ ደግሞ በእጅ" እንደሚለው የነ ዶ/ር ብርሃኑ ስሌት ሳይሆን፥ እኛ ወያነን
የመሰለ መሰሪና ድብቅ ኣጀንዳ ያለው ስርዓት በሰላማዊ ትግል መጣል ኣይቻልም ብለን ደምድመን፥ ቸርነቱ ከማያልቀው ፈጣሪያችን ዘንድ
በተለገሰን ጥበብ ከኣስራ ሶስት ዓመታት በፊት የዘየድነው ስልት ማዳመጥ ያልፈለጉ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ኣሁን ብድግ ብለው ይኸውና
በማይክሮስኮፕ ፈልገን ኣዲስ ስልት ኣግኝተንላችኋል ቢሉን እንደሌሎች የዋህ ፍጥረቶች የከበሮ ኣታሞ ኣብረን የምንመታ ኣይደለንም።
እነዶ/ር. ብርሃኑን ማስታወስ የምፈንልገው ነገር ቢኖር፥ እኛ ትደህይም ትበልፅግ ከኢትዮጵያ በቀር ሌላ የንተማመንበት
አገርም ዜግነትም የለንም። እንዲኖረንም ኣንመኝም። የተባረከችውና የተቀደሰችው ወድ ኣገራችን ልንኖርባት ባንታደልም፥ ቢያንስ ስንሞት፥
የቀብር ስነስርዓት ጋጋታ ሳያስፈልገን እንደ ታላቁ የጥበብ ሰው ወዳጄ ተስፋየ ለማ ሬሳችንን በእሳት እንዲቃጠል ተናዘን ከእሳት
የሚተርፈው ኣመድ ቅሪታችን ከኢትዮጵያ ቅዱስ ኣፈር ጋር ተደባልቆ የምንቀበርባት ብቸኛ ኣገራችን ስለሆነች እንደ ዓይናችን ብሌን
የምንሳሳላት መሆኑን ነው። ስለሆነም፥ ኣገሩ የኛና የመሰሎቻችን ብቻና ብቻ ኣገር ነውና፥ ኣገራችን ቤተ ሙከራ ትመስል ኣዳዲስ
መድኃኒቶች እየተፈለሰፉ እንድትጋት ስትደረግ ተቀምጠን የምንመለከት ፍጡራን ኣይደለንም። ለዚህም ነው፥ የማይሰራና የማያዋጣ ስራ
ስናይ ብድግ ብለን እሳት ወስጥ የምንገባው። በደርግ ውድቀት ዋዜማና በባድመ ጭቅጭቅ ማግስት ብድግ ብለን የገባነውም ከዲስኮ ቤት
ሳይሆን ከሚለበልብ እሳት ውስጥ ነው።
ይህ ማለት ግን፥ ግንቦት ሰባቶች ኣርፋችሁ ተቀመጡ ማለታችን ኣይደለም። እንዲያውም እኛ የምንጠላው እጁንና
እግሩን ኣጣጥፎ በመቀመጥ የኣዞ እንባ የሚያነባውን ና ስርቶ ሳያሳይ የሚሰሩትን ሲቦጭቅ የሚውለውን መካን ሰው ብቻ ነው። ስለሆነም፥
ድካማችሁና ድካማችን ፍሬ ኣፍርቶ ህዝባችን እፎይ ብሎ እኛም በቀረቺን ኣጭር ጊዜ ለኣገርና ለህዝብ ሲባል ያስቀየምናቸውና ለጥቅማቸው
ሲሉ ያስቀየሙን ሁሉ ይቅር ብለንና ንስሃ ገብተን ወደማይቀረው የፈጣሪያችን ቤት በሰላም እንድንጓዝ ከፈለጋችሁ እግዚኣብሔር ያሳየንን
ምክር እነሆ እናካፍላችሁ።

5
 ደራሲው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፥ ኣርታኢው/ኤዲተሩ ደግሞ ኣቶ ኣንዳርጋቸው ፅጌ የሆኑለት "የነፃነት ጎህ ሲቀድ" የመጨረሻው ምዕራፍ
15 "ገፅ 587-614) የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሆኔታ የትጥቅ ትግል እንደ ኣማራጭ የትግል ስልት ኣድርጎ መውሰድ ኣደገኛ መሆኑን ያትታል።
14

ከኤርትራ ህዝብና መንግስት ጋር መስራት ካለባችሁ ከላይ በተመለከተው መሰረት መለስ ዜናዊ ያልፈለገውና የጣለውን
የኤርትራ መንግስት ሃሳብ የራሳችሁ ኣድርጋችሁ ቀጥሉበት። እኛ ሌሎች እንደሚከተሉት የ"ባልበላውም እበትነዋለሁ" ዓይነት የዶሮ ፖለቲካ
ኣራማጆችና ተከታዮች ኣይደለንም። ያለ ምንም ተጨማሪ ግጭትና እልቂት የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ሊያስተሳስር የሚያስችል
ማንኛውም ተግባር ገብረማርያምም ያርገው ገመቹ፥ ሙስጦፋም ያርገው ዓብደላ፥ ኣልማዝም ታርገው ፋጡማ ምንም ችግር የለብንም።
ትግላችቹ በኣሳማኝ ፖለቲካዊ ግኝት ካልታጀበ በሚድያ ጋጋታና በጠመንጃ ጩኸት ብቻ ወያነን እንጥላለን የሚለው ስልታችሁ የትም
ስለማያደርስ እርሱት። እኛ ኣቅደነው በነበረውና ባማራ ኤሊቶች ከይሲ ሴራ የተጨናገፈውን መንገድ በጥበብ ተከተሉ። የኤርትራና
የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስተሳስር መንገድ በማያወላውል መንገድ ማረጋገጥ ከተቻለ ደግሞ፥ ወያነ ለድብቅ ዓላማው ሲል የበተነውን ኣገርና
ህዝብ ለምን ኣስተሳሰራችሁ ወይም ሰበሰባችሁ ብሎ የሚወጋችሁ ህዝብም ሆነ ሰራዊት በኢትዮጵያ ምድር ስለሌለ የጠመንጃውን ሁካታ
ትታችሁ ፖለቲካ ኣስቀድሙ። ሌሎች ጥቃቅን ምክሮችም ኣሉን ኣንካችሁ።
· ይህንን ማድረግ የሚቻለው ወያነ ከወደቀ በኋላ ነው የሚላችሁ ካለ፥ በዚያው በምታውቁት ያራዳ ቋንቋ "ቱሪስትህን
ብላ፤ ወያነ ከማናውቀው ዛፍ ተቆርጦ የተሰራ ጎባጣ ብትር ቢሆንም ኣስፈላጊ ብትራችን ነው።" በሉና የቅጩን ንገሩት።
· "ወያነና ሻዕቢያ ሁለቱም እኩል የኢትዮጵያ ጠላቶች ስለሆኑ ሁለቱም ባንዴ መጥፋት ኣለባቸው" የሚሉና ታላቁን
የኣማራ ህዝብ የማይወክሉ ነገር ግን የኣማራ ህዝብ ጠበቆች ነን ብለው የሚፏኣልሉ ስራፈት ያማራ ኤሊቶች ሲገጥሟችሁ፥ ፖለቲካ
ዕጣ ክፍላችሁ ኣይደለምና ሂዱና የፈረንጅ ከብት ፈልጋችሁ በእረኝነት ከብት ጠብቁ በሏቸው።
· በኣማራነትና "በንፁህ" ኢትዮጵያዊነት ተሸፍፍኖ ከወያነ ካዝና የሚቀላውጥ ሰው መሳይ ሰርጎ ገብ ኣማራ ሲገጥማችሁ
ደግሞ ከቻላችሁ በቦክስ ኣፍንጫውን በሉት፤ ካልተመቻችሁ ደግሞ ለጊዚያዊ ጥቅማ-ጥቅም ተብሎ ኢትዮጵያ ኣትሸጥም ኣትለወጥምና
ኣፈር ብላ ብላችሁ ሸኙት።
· እንደ ኣማሮቹ የወያነ "ፎርጅድ" ቲፎዞዎች ሳይሆኑ ስጋት የተጠናወታቸው የትግራይ ተወላጅ ኦርጂናል የወያነ
ቲፎዞዎችንም ስታገኙዋቸው "ኣይዟችሁ እኛ እንደ ኣለቆቻችሁ እንደነ መለስ/ስብሓት ቂመኞች፥ ዋልጌዎችና ገዳዮች ኣይደለንም፤
ኢትዮጵያን ለመታደግ እናንተን ማጥፋት ኣያስፈልገንም፤ ታላቁ ህዝባችን ደግሞ እንኳንና የተሳሳተ ወገኑን ቀርቶ የወራሪው ፋሺስት
ገዳይ ወታደሮችንና በንዳዎችን እንኳ ኣልተበቀለም፤ ላለፈው ጥፋታችሁ ባምላክም በሰውም ይቅር ተብላችኋል፥ ሌላ ጊዜ
ኣይልመድባችሁ፤ ኢትዮጵያን ማዳን የሚቻለው እናንተንም ሆነ ሌሎች ከናንተ በፊት የነበሩ ስርዓቶች መሪዎችና ተባባሪዎችንም
ማቀፍ ኣስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን እናንተም ተረዱት በሉና በፍቅር ኣስረዷቸው፤ ኣረጋጓቸው። ጥበበኞች ሁኑ።
በመጨረሻ የምናካፍላችሁ ወገናዊና ወሳኝ ምክርም ኣለን። ይህንን ከባድና ውስብስብ ያገራችን ጉዳይ የግንቦት ሰባት
ዶክተሮችና ጄኔራሎች ብቻቸውን ያከናውኑታል ብላችሁ ኣታስቡ። ስለዚህ፥ በተቻለ ፍጥነት ሁነኛ ያገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የተቃዋሚ
ድርጅቶች ኣሰባስቡና ኣብራችሁ ቀጥሉ። ታዲያ ጊዜ የለንምና ፈጠን ፈጠን በሉ። ቀናውን መስመር ከተከተላችሁ እኛም ቀድመን
እንደምንከተላችሁና ከጎናችህ እንደምንሰለፍ ኣትጠራጠሩ። ይህንን ወገናዊ ምክራችንን የማጣጣል መብታችሁ የተጠበቀ ሆኖ፥
እግዚኣብሔር ልቦና ይስጣችሁ። ይርዳችሁ። እግዚኣብሔር ልቦና ካልሰጣችሁና ካልረዳችሁ ግን ምን ይደረጋል። የሚቀረው ምርጫ፥
እናንተም እኛም መረብና ተከዜ ወንዝ ኣፋፍ ላይ መገናኘት ብቻ ነው። ዕድላችን ይህ ከሆነ፥ እንግዲህ ባንድ ነገር እንስማማ። እኛና እናንተ
ተታኩሰን የዕድል ጉዳይ ሆኖ ሳንሰዋ ብንቀርና ብትማርኩን ወይም ብንማርካችሁ ሁለታችንም ይቅር ይቅር ልንባባል ዛሬ እዚህ ዳያስፖራ
ሆነን ቃል እንግባ። በደህና ሰንብቱ።















No comments:

Post a Comment